የመሬት መንቀጥቀጡ እና ሊወሰድ ይገባል የተባለው ቀጣይ ጥንቃቄ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 2017የመሬት መንቀጥቀጡ እና ቀጣይ ጥንቃቄው
በአፋር ዞን ሶስት አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች እንዲሁም በአጎራባች ክልሎች የተከሰተው ከፍተኛ ስጋት የደቀነው የመሬት መንቀጥቀት ባለፉት 24 ሰዓታት መቀዛቀዝ ብያሳይም መዘናጋት እንዳይፈጥር ጥሪ ቀረበ፡፡
የአከባቢው ነዋሪዎች እና ባለሙያ ባለፉት 24 ሰዓታት የመሬት መንቀጥቀጡ መጠነኛ መቀነስ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
በአከባቢው የተፈጠረውን ስጋት ተከትሎ ነዋሪዎችን የማንሳት ስራ ግን እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
“መንቀትቀጡ ቀንሷል ትናንትና፡፡ ሌሊቱን ዘጠን ሰኣት አከባቢ ነው ትልሽ ከፍ ያለ መጠን መንቀትቀጥ የሰማነው፡፡ ከሰሞኑ የተሸለ ነገር አለ፡፡ አሁን ከነጋም ትንሽ ንዝረት እንጂ የከፋ ነገር አላስተዋልንም” ይህን ያሉት የአፋር ክልል አዋሽ ፈንታለ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡
የባለፉት 24 ሰዓታት የመሬት መንቀጥቀጥ መጠነኛ መቀነስ ቀጣይ ነውን?
ይህን የአከባቢው ነዋሪን አስተያየት ባለሙያም ይጋራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ሳይንስ ምርምር ተቋም የሶስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የመሬት መንቀጥቀጥ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ለዶቼ ቬለ እንደነገሩት ባለፉት 24 ሰዓታት ፋታ የማይሰጠው የአዋሽ አከባቢው የመሬት መንቀጥቀጥ መጠነኛ መረጋጋት ያሳየ መስሏል ነው የሚሉት፡፡ “እንዲሁ ቶሎ ሊወራ ልደመደም ባይገባም ዛሬና ትናት ትንሽ ሰብሰብ ያለ መስሏል” በማለት ምንም እንኳ እንቅስቃሴውን ብቀጥልም የመንቀጥቀጥ መጠኑና ድግግሞሹ ቀንሷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ባለሙያው እንደሚሉት ጭስና የፈላ ውሃ ከጭቃ ጋር ወደ ሰማይ ስንፎለፎሉ በታየባቸው የአፋር ምድር እስካሁን ድረስ ባለው “ላቫ” የሚባለው ቅልጥ አለት አልወጣም፡፡ “እስካሁን የተመለከትነው የታመቀ ፍልውሃ ነው እንጂ ላቫ አልወጣም” ሲሉም ማረጋገቻ ሰጥተዋል፡፡
የተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ ምልክት በአፋር ክልል
ባለፈው ሳምንት በአፋር ክልል ዞን 03 ዱለቻ እና አዋሽ ፈንታሌ በተባሉ ሁለት ወረዳዎች እና አዋሳኝ ላይ ባሉ ክልሎች በበርካታ ቀበሌዎች ሳምንቱን በሙሉ በመጠንም ሆነ በድግግሞሹ ከፍ ብሎ የታየው ርዕደ መሬት ከፍተኛ የቤቶች መፈራረስ ጉዳትም በማስከተሉ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ጀምሮ ከነዚሁ አከባቢዎች ነዋሪዎችን የማሸሽ ስራ መሰራት መጀመሩን የኢትዮጵያ መንግስት በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር በኩል አስታውቆ ነበር፡፡
ለተፈናቃዮች የተሰጠ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ትኩረት
ዶይቼ ቬለ ከአከባቢው እስካሁን የተነሱት ማህበረሰብ ቁጥር እና የተደረገውን ድጋፍ በተመለከተ ለኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባይ እና ለአፋር ዞን ሶስት ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዶ አሊ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ቢያደርግልቻውም ለማብራሪያው ፈቃደኝነታቸውን አላገኘም፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ እና የኢትዮ - ጅቡቲ መስመር ኹኔታ
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ቅዳሜ ለት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ግን በአፋር ክልል ዞን 03 ከአዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ ተጋላጭ ተብለው ከተለዩ ቀበሌያት ነዋሪዎችን በማስወጣት ሌላ ቦታ ማስፈር መጀመሩን አሳውቆ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ እስካሁን 70 ሺህ ግድም ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ የወጠነ ከ280 ሚሊየን በላይ የሚገመት የምግብ-ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ ወደ አከባቢው ማጓጓዝ መጀመሩን ጠቁሟልም፡፡
ይህንኑን የመንግስት የነዋሪዎችን የማሸሽና ድጋፍ ስራዎችን መመልከታቸውን የሚገልጹት የአፋር አዋሽ ፈንታሌ ወረዳው አስተያየት ሰጪ በተለይም ከዱለቻ ወረዳ ቀሰም ስኳር ፋብሪካ ዙሪያ እና ሌሎችም ስፍራ የተፈናቀሉ 5 ሺህ አባወራዎች በአሚባራ ወረዳ በተሰናዳው መጠለያ መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡ “መንግስት ተፈናቃዮችን ቀበና ከተባለ ቀሰም ስኳር ፋብሪካ አከባቢ በአገር መከላከያ ሰራዊት ኦራል እያመላለሰ ወደ አሚባራ ወረዳ እያሻገራቸው እንደሆነ በአይነ ተመልክቻለሁ” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ በዚህ አሚባራ ወረዳ ለደረሱ የምግብ ድጋፍ ስደረግላቸው ማየታቸውንም አስረድተዋል፡፡
ምን ልከሰት ይችላል?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ሳይንስ ምርምር ተቋም የሶስሞሎጂ ትምህርት ክፍል የመሬት መንቀጥቀጥ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አታላይ አየለ፤ አሁን ላይ በአፋር ክልል ሁለት ወረዳዎች አስደንጋጭ ሆኖ የታየው የመሬት መንቀጥቀጥ መንስኤዎች መዳረሻቸው ለመተንባይ ባይቻልም ሶስት የይሆናል መላምቶችን የሚሰጥ ነው ባይ ናቸው፡፡ “አንደኛው የተጠራቀመ ኃይል ስለሆነ በመሬት ውስጥ የሞገድ ኃይሉን እየቀነሰ እየተሰበረ የሚሄድ ከሆኑ ቅልጥ ኣለቱ ውስጥ በመቅረት መሬት ውስጥ አለት ልፈጥር ይችላል፡፡ ሁለተኛው የይሆናል ግምት ቅልት አለቱ ወጥቶ ብዙም ሳይርቅ በዚያው ልፈስ ይችላል የሚል ሲሆን ሌላኛው አደገኛ ክስተት ሊሆን የምችለው ቅልጥ አለቱ ስፈነዳ አከባቢው ላይ ያገኘውን ከማቃጠል ጀምሮ ወደ ጂቡቲ የሚወስደውን አውራ ጎዳና የመዝጋት እድል ይኖረዋል የሚል ነው” ሲሉ አስፈላጊው ጥንቃቄ ግን እንዲወሰድ አሳስበዋል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጡ ለአዲስ አበባ ስጋት ነውን?
ባለፈው ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆ ከፍ ባለ መጠን የተሰማው የመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት አዋሽ አከባቢ የተፈጠረውን 5.8 ሬክተርስከል የሚለካ የመሬት መንቀጥቀጥን ተከትሎ ነው፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ መጠኑ ከዚህስ ከፍ ቢል አዲስ አበባን ለመሳሰሉ በመቶዎች ኪ.ሜ ርቀት ላይ ለሚገኙ ከተሞች አስጊ ነው ወይ በሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው ባለሙያው፤ እድሉ አነስተና ቢሆንም አይሆንም ሚል ማስተማመኛ መስጠት ግን እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ “ትንሽ መጠነና ጉዳት ቢያደርስ ነው ብለን ነው የምናስበው” በማለት ግን ደግሞ በ1995 ሳይገመት ሜክሲኮ ሲቲን የመታው ከሩቅ የተፈጠረ መሬት መንቀጥቀጥ በማስታወስ ከወዲሁ ግንዛቤዎችን በማስፋት ጥንቃቄ እንዲደረግ በአጽኖት አሳስበዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ