1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«መሬት ከመንቀጥቀጥም አልፎ እያዘለለችን ነው»

ሥዩም ጌቱ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 26 2017

በተለይም በሰጋንቶ ቀበሌ የመሬት መንቀጥቀጡ “የሚውረገረግ” ሲሉ ክብደቱን ገልጸውታል፡፡

https://p.dw.com/p/4oocN
አደገኛ ስጋት እየደቀነ የመጣው የመሬት መንቀጥቀጥ
አደገኛ ስጋት እየደቀነ የመጣው የመሬት መንቀጥቀጥምስል Seyoum Getu/DW

የቀጠለው የመሬት መንቀጥቀጥ

አደገኛ ስጋት እየደቀነ የመጣው የመሬት መንቀጥቀጥ
በኢትዮጵያ ውስጥ በሶስት ክልሎች አዋሳኝ ማለትም አፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎችን በሚያገናኘው ስምጥ ሸለቆና ዙሪያው ባሉ አከባቢዎች እየከፋ የመጣው የመሬት መንቀጥቀጥ አሁን አሁን ወደ ሚያሰጋ ደረጃ እየተሸጋገረ መስሏል፡፡
በነዚህ አከባቢዎች በአዋሽ፣ አንኮበር፣ ሚኤሶ እና አቦምሳ ድረስ ከ5.2 እስከ 5.8 ረክተርስኬል የሚለካ ርዕደመሬት ሌሊቱን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 9፡52 ላይ መከሰቱን በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ተቋማት እየገለጹ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር በኩል ዛሬ ይፋ እንዳደረገው በመጀመሪያው ምዕራፍ ከሶስቱ ክልሎች አዋሳኝ ላይ ካሉ 12 ቀበሌያት 80 ሺህ ግድም ዜጎችን ለማንሳት ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ሌሊቱን 9፡52 በአፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ አከባቢዎች የተከሰተው ርዕደ መሬት አዲስ አበባ እና ሌሎችም ከተሞች ድረስ ዘልቆ በፈጠረው እጅግ ከባድና ዘለግ ላሉ ሰከንዶች በቆየው ንዝረት ዜጎች የከፋ ድንጋጤ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ 


የርዕደ መሬቱ መነሻ ስፋራዎቹ ምን ላይ ናቸው?
በአፋር አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ በተባሉ ሁለት የገቢረሱ (ዞን 03) ወረዳዎች እጅጉን ተደጋግሞ አከባቢው ላይ አደጋ ማስከተሉን የገፋበት መንቀጥቀጡ፤ አስቀድሞም ለመፈናቀል የተገደዱትን የአከባቢው ነዋሪዎችን አሁን ላይ ተስፋ ያስቆረጠ መስሏል፡፡ ዛሬ አስተያየታቸውን ለዶይቼቨለ የሰጡ የዱለቻ ወረዳ ዱሩፉሊ ቀበሌ ነዋሪ እሳቸውን ጨምሮ ተስፋ ባለመቁረጥ በአከባቢው ቀርተው የነበሩ ነዋሪዎችም ጭምር እቃዎቻቸውን እየሸከፉ አከባቢውን የመልቀቅ ጉዞ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡ “ሰው ሁሉ ተፈናቅሎ ንብረት እያወጣን ነው አሁን፡፡ ከዱለቻ ወረዳ ሳጋንቶና ድሩፉሊ ቀበሌ እንዲሁም ከአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ እና ቀበና ቀበሌ ሰው በሙሉ ተነስቷል” ብለዋል፡፡
ዛሬ እኩለ ቀን እቃውን እየጫኑ ባለበት ሰዓት እንኳ መሬት ከመንቀጥቀጥም አልፎ እያዘለለችን ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ እንደ ትናንቱ ሁሉ በፈንታሌ እና ዶፋን ተራራ መካከል ባለው ሳጋንቶ ቀበሌ እንደ ፍልውሃ ጭስ እና ጭቃ እንዲሁም ቅባታማ ሙቅ ውሃን ሚተፋው እሳት ዛሬም ቀጥሎ መታየቱን ገልጸዋል፡፡

በፈንታሌ እና ዶፋን ተራራ መካከል ባለው ሳጋንቶ ቀበሌ እንደ ፍልውሃ ጭስ እና ጭቃ እንዲሁም ቅባታማ ሙቅ ውሃን ሚተፋው እሳት ዛሬም ቀጥሎ መታየቱን ገልጸዋል፡፡
በፈንታሌ እና ዶፋን ተራራ መካከል ባለው ሳጋንቶ ቀበሌ እንደ ፍልውሃ ጭስ እና ጭቃ እንዲሁም ቅባታማ ሙቅ ውሃን ሚተፋው እሳት ዛሬም ቀጥሎ መታየቱን ገልጸዋል፡፡ምስል Seyoum Getu/DW


የቀሰም ስኳር ፋብሪካ አስተዳደርና መኖሪያ ህንፃዎች መፍረስ 
ሌላው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የቀሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሊ ሀሰን፤ “አዳር በነበረው ከፍተኛ መንቀትቀጥ የፋብሪካው መኖሪያ እና ቢሮ ህንታዎች ሙሉ በሙሉ ፈራርሷል” ብለዋል፡፡ በአከባቢው ላይ የነበሩትን ነዋሪዎች ከአገር መከላከያ እና ከተቋቋመው የአደጋ ጊዜ ኮሚቴ ጋር የፋብሪካው ማህበረሰብ እና የአከባቢውን ነዋሪ የማስወጣት ስራ ትናንት ሲከወን ውሏል የሚሉት ስራ አስፈጻሚው፤ ትናንት ከወትሮም ጠንክሮ የታየው ርዕደ መሬት ከህንጻው በተጨማሪ በህንጻዎቹ ውስጥ የነበሩ ኮምፒዩተሮችና ሌሎች እቃዎችን ከጥቅም ውጪ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
አንገብጋቢው ነዋሪዎችን ከአደጋው የማራቅ ጉዳይ
እስከአሁን በመሬት መንቀጥቀጡ በህይወት ላይ የደረሰ አደጋ አለመሰማቱን የገለጹት አቶ አሊ፤ ፋብሪካው ስራ ለማቆም መገደዱን ግን ጠቁመዋል፡፡ “በመሬት መንቀጥቀጡ ይህ አከባቢ የስጋት ቀጠና መሆኑ ከተገለጸ በኋላ አብዛኞቹን ሰራተኞች አስቀድሞም አስወጥተናል” ነው ያሉት፡፡ አክለውም በተለይም በሰጋንቶ ቀበሌ የመሬት መንቀጥቀጡ “የሚውረገረግ” ሲሉ ክብደቱን ገልጸውታል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ሳይንስ ምርምር ተቋም የሶስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የመሬት መንቀጥቀጥ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ፤ ጭቃና ፍልውሃን ሲተፋ የነበረው የትናንቱ ክስተት እስካሁን ቅልጥ አለት ለማፍሰሱ ማረጋገጫ አልሰጡም፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት የተጋራውን አከባቢው ላይ ቅልት አለት እንዳፈነዳ ተደርጎ የተጋራውንም መረጃ የማይታመንና ያልተጣራ ነው ብለውታል፡፡ 
በጉዳዩ ላይ ዛሬ መግለጫ ያወጣው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር መንግሥት የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶቹን በዘርፉ ባለሙያዎች በቅርበት በመከታተል የርዕደ መሬቱ ማዕከል ከሆኑ አካባቢዎች ነዋሪዎችን የማራቅ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ አገልግሎቱ መንግስት በአከባቢው 12 የአደጋ ቀጠና ቀበሌዎች ለይቶ ለ80 ሺህ ዜጎች ቅድሚያ በመስጠት ከአካባቢው በማራቅ ለማስፈር ርብርብ ላይ ነውም ብሏል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር