1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመብት ጥሰት በትግራይ ተወላጅ የፖሊስ አባላት ላይ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 25 2016

ከሰሜኑ ጦርነት በፊት በፌዴራልና በአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም በትግራይ ክልል የፀጥታ ተቋማት ላይ ያገለግሉ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የፖሊስ አባላት ላይ የመብት ጥሰት አሁን ድረስ እየደረሰባቸው ነው ሲል ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች - በኢትዮጵያ የተባለ የሲቪክ ድርጅት ገለፀ።

https://p.dw.com/p/4ZoLc
ወታደሮች ቁጭ ብለው
ከሰሜኑ ጦርነት በፊት በፌዴራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም በትግራይ ክልል የፀጥታ ተቋማት ላይ ያገለግሉ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የፖሊስ አባላት ላይ የመብት ጥሰት አሁን ድረስ እየደረሰባቸው ነው ሲል ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች - በኢትዮጵያ የተባለ የሲቪክ ድርጅት ገለፀ።ምስል Solomon Muchie/DW

ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች - በኢትዮጵያ የሲቪክ ድርጅት

ከሰሜኑ ጦርነት በፊት በፌዴራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም በትግራይ ክልል የፀጥታ ተቋማት ላይ ያገለግሉ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የፖሊስ አባላት ላይ የመብት ጥሰት አሁን ድረስ እየደረሰባቸው ነው ሲል ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች - በኢትዮጵያ የተባለ የሲቪክ ድርጅት ገለፀ።  የሲቪክ ድርጅቱ በጦርነቱ ወቅት ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በሚል ሕጋዊነቱን አጥቷል ባለው የትግራይ ክልል ምክር ቤት በወጣ ዐዋጅ መሰረት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ከ 1 ሺህ በላይ የትግራይ ክልል ፖሊስ አባላት የነበሩ ሰዎች ከሥራ ተባረው በችግር ላይ ናቸው ሲል ገልጿል።  እነዚህ የቀድሞ የክልሉ የፖሊስ አባላት በጦርነቱ ወቅት ከሕወኃት ጎን አልተሰለፋችሁም በሚል ምክንያት ለመብት ጥሰት የተጋለጡ ስለመሆናቸውም ተነግሯል። 

የሲቪክ ድርጅቱ በአዲስ አበባ እና በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ ይሰሩ የነበሩና በጦርነቱ ወቅት ተይዘው ታሥረው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላት ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ አለመደረጉንም ዛሬ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።  የፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ቢተገበር ይህ ችግር ይፈታል ያለው የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ያቀረበውን ይህን ሪፖርት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳልተቀበለው እና ከትግራይ እና ከፌዴራል ፖሊስ ግን ምንም ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል።  

ጠመንጃ የያዘ ሰው
የቀድሞ የክልሉ የፖሊስ አባላት በጦርነቱ ወቅት ከሕወኃት ጎን አልተሰለፋችሁም በሚል ምክንያት ለመብት ጥሰት የተጋለጡ ስለመሆናቸውም ተነግሯል። ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images


ከሰሜን ኢትዮጵያው አውዳሚ ጦርነት በፊት በፌዴራልም ሆነ በአዲስ አበባ እንዲሁም ቁጥራቸው የላቀ ነው የተባሉት በትግራይ ክልል በፖሊስነት ያገለግሉ የነበሩ የቀድሞ አባላት ለዚህ ሁሉ ከሥራ የመታገድ፣ የሥነ ልቦና ጉዳትም ይሁን ሌሎች ችግሮች ሰለባ ቢሆኑ በጦርነቱ ምክንያት በመሆኑ ፣ ጦርነቱን የቋጨው ስምምነት በትክክል ይተግበር ሲል ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች - በኢትዮጵያ የተባለ የሲቪክ ድርጅት ዛሬ ጠይቋል። 
የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መብርሂ ብርሃነ የስምምነቱ ፈራሚዎች ስምምነቱን በትክክል ያክብሩ ብለዋል።

የትግራይ ተወላጅ የፖሊስ አባላት

በትግራይ ክልል የቀድሞው ምክር ቤት የወጣ አዋጅ እነዚህን ሰዎች ወደ ሥራ እንዳይመለሱ እግድ ቢጥልም ይህንን አዋጅ ተመስርቶ ርምጃ መውሰድ አይቻልም ሲሉ ኃላፊው ገልፀዋል።

ይህ አዋጅ በሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ እና በፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲሻር ለማድረግ በቀጣይ ድርጅታቸው  እንደሚንቀሳቀስና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዘው እንደሚሃዱም ኃላፊው ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ጦርነቱ በተቀሰቀ ማግስት ማንነታቸው ተለይቶ ስለመታሰራቸው፣ ከዚያ በኋላ  ወደ ሥራ አለመመለሳቸው የስምምነቱን መርህ የሚጥስ በመሆኑ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ተጠይቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የቀረበውን ሪፖርት ከተመለከቱ በኋላ አንቀበልም ስለማለታቸው ይህ የሲቪክ ድርጅት ተናግሯል። ከፌዴራል ፖሊስ እና ከትግራይ ክልል ግን እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኙ አስታውቋል።
የሲቪክ ድርጅቱ ስላነሳው ጉዳይ ከሦስቱም አካላት በስልክ ምላሽ ለማግኘት ጥረት አድርገናል። ምላሽ ግን ልናገኝ አልቻልንም።

ሰሎሞን ሙጬ
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ