1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 30 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 30 2017

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 26,000 ሯጮች በተሳተፉበት የጉዋንጁ ማራቶን ክብረወሰን በመስበር ድል ተቀዳጅተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የአርሰናል እና የማንቸስተር ሲቲ ነጥብ መጣል ለቸልሲ መልካም አጋጣሚ ሁኗል ። ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሊቨርፑልን በ4 ነጥብ ተጠግቷል ።

https://p.dw.com/p/4nwC9
Deutschland Bundesliga  St. Pauli vs Holstein Kiel
ምስል Cathrin Mueller/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 26,000 ሯጮች በተሳተፉበት የጉዋንጁ ማራቶን ክብረወሰን በመስበር ድል ተቀዳጅተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የአርሰናል እና የማንቸስተር ሲቲ ነጥብ መጣል ለቸልሲ መልካም አጋጣሚ ሁኗል ። ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሊቨርፑልን በ4 ነጥብ ተጠግቷል ። ማንቸስተር ዩናይትድ በገዛ ሜዳው መሸነፉ ደጋፊዎቹን አስደንግጧል ። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽን ዳግም ድል ሲቀናው ጃማል ሙሳይላ የቡድኑ ዳግም ወሳኝ ተጨዋችነቱን አስመስክሯል ።  ባዬርን ሌቨርኩሰን እና ላይፕትሲሽ ሲያሸንፉ፤ አይንትራኅት ፍራንክፉርት እና ዶርትሙንድ ነጥብ ጥለዋል ። 18 የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ ። በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር አርቲስቶች ተመረጡ መባሉ አወዛግቧል ። 

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 26,000 ሯጮች በተሳተፉበት የጉዋንጁ ማራቶን በወንድም በሴትም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃዎችን ጠቅልለው በመውሰድ ድል ተቀዳጅተዋል ። ቻይና ውስጥ ትናንት በተከናወነው የማራቶን ሩጫ ፉክክር፦ ኢትዮጵያዊው ሯጭ ሌሊሳ ገቢሴ 2:06:28 በመሮጥ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቦ አንደኛ ወጥቷል ። በሴቶች ተመሳሳይ የሩጫ ውድድርም፥ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አንቺዓለም ሃይማኖት 2:25:13 በመሮጥ አሸንፋለች ።

በወንዶች ፉክክር፦ በላይ አስፋው እና አሠፋ መንግሥቱ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። በመሃከል አራተኛ ኬኒያዊው ፌሊክስ ኪርዋ ጣልቃ ገብቶ አምስተኛ ደረጃም በኢትዮጵያዊው አትሌት መኳንንት ዐየነው ተይዟል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አንዷለም በላይ ኬንያዊው ፒዩስ ካራንጃን ተከትሎ በ8ኛ ደረጃ አጠናቋል ። በውድድሩ ከ10ኛ እስከ 20ኛ ተከታትለው የገቡት ቻይናውያን ናቸው ።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጉዋንጁ ማራቶን በወንድም በሴትም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃዎችን ጠቅልለው በመውሰድ ድል ተቀዳጅተዋል
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጉዋንጁ ማራቶን በወንድም በሴትም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃዎችን ጠቅልለው በመውሰድ ድል ተቀዳጅተዋል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Florian Gaul/greatif/picture alliance

በሴቶች ፉክክር ደግሞ፦ ኢትዮጵያውያቱ ቸርነት ምሥጋናው እና ሮማን ግደይ አንቺዓለምን ተከትለው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል ። አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃን አውስትራሊያዊቷ ሊዛ ዋይግትማን እና ኬንያዊቷ ጃኔት ሩጉሩ አግኝተዋል ። ጠጅነሽ ገቢሳ እና ለተብርሃን ኃይላይ ስድስተኛ እና 12ኛ ሆነው አጠናቀዋል ። ቀሪዎቹ ቦታዎች እስከ 20ኛ ድረስ በቻይናውያን አትሌቶች የተያዘ ነው። የኅዳር 23 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

አወዛጋቢው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ አርቲስት መምረጡ በበርካቶች ዘንድ ውዥንብር እና ጥያቄ አጭሯል ። የተመረጡት እነማን ናቸው፤ ውዝግቡስ የተነሳበት ምክንያት ምንድን ነው? የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ፦ የውዝግቡ መንስዔ አርቲስቶች በአመራርነት መመረጣቸው ነው ብሏል ። 

በርካቶች በዶይቸ ቬለ የቀጥታ ሥርጭት ላይ ስለ ምርጫው ግራ በመጋባት ማብራሪያ እንፈልልጋለን ሲሉ ጠይቀውን ነበር ። ምርጫው የተካሄደው በምን መልኩ ነው? አርቲስት ማስተዋል ወንደሰንስ እንዴት የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሁና ተመረጠች? አርቲስት ማስተዋልም ሆነች ሌሎች የተመረጡት በወዳቸው ተወክለው ከመጡ በኋላ ነው መባሉን ዖምና አክሏል ። 

የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ
የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለምስል privat

ከምርጫው በኋላ የተናገረችው ተብሎ በማኅበራዊ መገናኛ አውታር በተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ዋነኛው አስፈላጊ ነገር የገንዘብ ድጋፍ ነው ብላለች ። ያንንም፦ ከባለሃብቶችና እንዲሁም ኤምባሲዎች ጋር በመነጋገር ገቢ ለማምጣት ማሰቧን ተናግራለች ። ስታዲየም ውስጥ የሚገቡ ድጋፍም የሚያደርጉ ሴቶች እንዳሉ ይታወቃል ።  ሆኖም ዖምና አርቲስቷ በእግር ኳሱ ዘርፍ ከዚህ ቀደም ዐትታወቅምr ብሏል።  

ፕሬሚየር ሊግ

በመጥፎ የአየር ሁኔታ ከኤቨርተን ጋር የነበረው ግጥሚያው ለሌላ ጊዜ የተላለፈበት ሊቨርፑል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በደረጃ ሰንጠረዡ መሪነት ላይ እንደሰፈረ ነው ።  ሊቨርፑል አንድ ተስካካይ ጨዋታ እየቀረው በ35 ነጥብ ፕሬሚየር ሊጉን ይመራል ። ትናንት ቶትንሀምን በገዛ ሜዳው 4 ለ3 ያሸነፈው ቸልሲ በ31 ነጥብ ይከተላል ። የማንቸስተር ሲቲው ኧርሊንግ ኦላንድ እና የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሣላኅ በ13 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ኮከብ ግብ አግቢነቱን ይመራሉ ። ትናንት ሁለት ግቦችን በፍጹም ቅጣት ምቶች ያስቆጠረው የቸልሲው ኮል ፖልመር በ11 ይከተላቸዋል ። የኅዳር 16 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

አርሰናል ከፉልሀም ጋር ገጥሞ አንድ እኩል በመለያየት በ29 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ከክሪስታል ፓላስ ጋር ሁለት እኩል በመለያየት በጥብ የጣለው ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ በ27 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ማንቸስተር ዩናይትድን በሜዳው 3 ለ2 ጉድ ያደረገው ኖቲንግሀም ፎረስት 25 ነጥብ ሰብስቦ የፕሬሚየር ሊጉን አምስተኛ ደረጃ መቆናጠጥ ችሏል ።  በሜዳው ሽንፈት የገጠመው ማንቸስተር ዩናይትድ በ19 ነጥቡ 13ኛ ደረጃ ላይ አሽቆልቁሎ ይገኛል ። ኖቲንግሀም ፎረስት ከ1994 ወዲህ ማንቸስተር ዩናይትድን በፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ በሜዳው ኦልድ ኦትራፎርድ ሲያሸንፈው የቅዳሜው የመጀመሪያው ነው ።  ዛሬ ማታ ዌስትሀም ከዉልቭስ ጋር ይጋጠማል ።

ጃማል ሙሳይላ ተቀይሮ በመግባት ለባዬርን ሙይንሽ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል
ጃማል ሙሳይላ ተቀይሮ በመግባት ለባዬርን ሙይንሽ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል ። ወሳኝ ተጨዋችነቱን ዳግም አስመስክሯል ምስል Harry Langer/DeFodi Images/picture alliance

ቡንደስ ሊጋ

ጃማል ሙሳይላ ተቀይሮ በመግባት ለባዬርን ሙይንሽ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል ። ባዬርን ሙይንሽን በትናንቱ ግጥሚያ ሐይደንሐይምን 4 ለ2 ሲያሸንፍ ሁለቱን ተጨማሪ ግቦች ያስቆጠሩት ዳዮት ኡማዬካኖ የመጀመሪያዋን እንዲሁም ሌዮን ጎሬትስካ የማሳረጊያዋን ናቸው ። ባዬርን ሙይንሽን የትናንቱ ድል ተጨምሮ ቡንደስሊጋውን በ33 ነጥብ ይመራል ። ከአውግስቡርግ ጋር ሁለት እኩል የተለያየው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ27 ነጥብ ይከተላል ። በ26 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባዬርን ሌቨርኩሰን ቅዳሜ ዕለት ሳንክት ፓውሊን አስተናግዶ 2 ለ1 ሸኝቷል ። 24 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ በሆልሽታይን ኪዬል አስደንጋጭ የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል ። የኅዳር 09 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ቮልፍስቡርግ እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ በተመሳሳይ 21 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያአምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ቮልፍስቡርግ ትናንት ማይንትስን 4 ለ3 ሲያሸንፍ፤ ወደ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ያቀናው ቦሩስያ ዶርትሙንድ አንድ እኩል ተለያይቷል ።  ሐይደንሐይም፤ ሆልሽታይን ኪዬል እና ቦሁም ከ16ኛ እስከ 18ኛ የመጨረሻ ደረጃ  ወራጅ ቀጣና ውስጥ ተደርድረዋል ።

ሐንጋሪ ቡዳፔስት የሚገኘው ፑካሽ አሬና ስታዲየም
ነገ እና ከነገ በስትያ 18 የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ምስል Trenka Atilla/empics/picture alliance

 ሻምፒዮንስ ሊግ

ነገ እና ከነገ በስትያ 18 የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ። ነገ ከሚኖሩ ዘጠኝ ግጥሚያዎች መካከል ሦስቱ በጀርመን ቡንደስ ሊጋ መሪነት ተርታ የተሰለፉ ቡድኖች የሚሳተፉበት ነው ። መሪው ባዬርን ሙይንሽን በጦርነት የተዳቀቀችው ዩክሬን ቡድን ሻካታር ዶኒዬትስክን ይገጥማል ። ጨዋታው የሚካሄደው ጀርመን ውስጥ በሻልከ 04 ስታዲየም ቬልትኒስ አሬና ነው ። ባዬርን ሌቨርኩሰንም በሜዳው ባሽ አሬና ስታዲየም የጣሊያኑ ኢንተር ሚላንን ይገጥማል ። ኤርቤ ላይፕትሲሽ ሬድ ቡል አሬና ስታዲየሙ ስውጥ የእንግሊዙ አስቶን ቪላን ያስተናግዳል ። ጨዋታዎቹ በአጠቃላይ በተመሳሳይ ሰአት ነው የሚከናወኑት ። ከረቡዕ ግጥሚኢዎች መካከል ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከባርሴሎና፤ አርሰናል ከሞናኮ፤ አትላንታ ከሪያል ማድሪድ እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪስ ከስሎቫን ብራቲስላቫ ጋር የሚያደርጓቸው ይገኙበታል ።የኅዳር 02 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ጀርመን ለሣዑዲ ዓረቢያ

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2034 የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ ለምትጥረው ሣዑዲ ዓረቢያ ድጋፍ እንደምታደርግ ዐሳውቃለች ። ይህንም የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል ። ጀርመን በሰብአዊ መብቶች እና ዴሞክራሲ ረገድ በርካታ ትችቶች ለሚቀርቡባት ሣዑዲ ዓረቢያ ድጋፍ ማድረጓ ከጀርመን ቡድን ደጋፊዎች እና ተጨዋቾች ጭምር ነቀፌታ አስከትሏል ።

 ቤርንድ ኖየንዶርፍ (በቀኝ ያሉት) የፊፋን በ2030 እና 2034   የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር ምርጫን ይደግፋሉ
ቤርንድ ኖየንዶርፍ (በቀኝ ያሉት) የፊፋን በ2030 እና 2034 የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር ምርጫን ይደግፋሉ ምስል Federico Gambarini/dpa/picture alliance

የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚደንት ቤርንድ ኖየንዶርፍ፦ «በተሳሳተ መንገድ ላይ ነን የሚል አንድም ድምፅ አልነበረም» ብለዋል ጠቅላላ የእግር ኳስ ማኅበራት በውሳኔው መስማማታቸውን በመግለጥ ። በዚህም መሠረት ጀርመን ከሣዑዲ ዓረቢያ ቀደም ብለው በጥምር ለሚያዘጋጁት ሦስት ሃገራትም ድጋፏን ገልጣለች ። የ2030 የዓለም ዋንጫን በዋናነት ሞሮኮ፣ ስፔን እና ፖርቹጋል በጋራ ለማሰናዳት ደፋ ቀና እያሉ ነው ። የሁለቱንም የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ መሰናዶዎች አስተናጋጅነት ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (FIFA) ውሳኔ ይሰጥበታል ። አርጀንቲና፣ ፓራጓይ እና ዑራጓይም የ2030 የዐለም ዋንጫን በጋራ ለማሰናዳት ፍላጎት አላቸው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti