1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህዝቡን ከሀገሩ ያፈናቀለው የሞዛምቢኩ ምርጫ ውጤት

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 26 2017

የማላዊ ባለሥልጣናት የሞዛምቢክ ስደተኞችን የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ለማጥናት ከተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህጻሩ UNHCR ጋር እየሰሩ መሆኑን አረጋግጠዋል። ሆኖም ማላዊ የራሷን ዜጎችና አሁን በሀገርዋ የሚገኙ ቁጥራቸው ወደ 54ሺህ የሚጠጋ ስደተኖችን ለመመገብ በመታገል ላይ ያለች የምግብ እጥረት ያለባት ሀገር ናት።

https://p.dw.com/p/4oo1y
Mosambik Proteste in Maputo
ምስል Amilton Neves/AFP

ህዝቡን ከሀገሩ ያፈናቀለው የሞዛምቢኩ ምርጫ ውጤት

 
ከሞዛምቢኩ ምርጫ በኋላ በተነሳው ብጥብጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎረቤት ማላዊ ሸሽተዋል። ህዝቡ ሀገሩን ለቆ መውጣት የጀመረው በጥቅምት የተካሄደውን ምርጫ ገዥው የፍሬሊሞ ፓርቲ ማሸነፉን የሀገሪቱ ሕገ መንግስታዊ ሸንጎ ካረጋገጠ በኋላ ነው።  የተጭበረበረ ሲሉ ታቃዋሚዎች ያወገዙትን የምርጫ ውጤት ከፍተኛ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ሲያጸድቅ ተቃውሞ ፣ንብረት ማውደምና መዝረፍ ተባባሰ። ኤሌን ኮሳ በማላዊ ደቡባዊ ድንበር ላይ በሚገኘው በንሳንየ ቀበሌ ከተጠለሉት ከ13 ሺህ በላይ ስደተኞች አንዷ ናቸው። እርሳቸውና ሌሎች የቤተሰቦቻቸው አባላት ፍርድ ቤት የምርጫ ውጤቱን ሲቀበል ነበር መኖሪያቸውን ጥለው የተሰደዱት።

ምርጫን ተከትሎ በሞዛምቢክ የቀሰቀሰው ተቃውሞ
 «እዚህ የደረስኩት ሰኞ በጎርጎሮሳዊው ታኅሳስ 23 ቀን ነው። በፖለቲካውን አለመረጋጋት ምክንያት እንደተሰደዱት ሌሎች ሰዎች ሁሉ እኔም በዚህ መጠለያ ውስጥ ችግሮች ይደርሱብናል። ከሰኞ ጀምሮ አልበላሁም፤ልጆች አሉኝ ። ሌሎች እርጉዝ ሴቶች ፣አዛውንቶች የአካል ጉዳተኞችም አሉ። መጸዳጃ ቤት ፣ውሐ እና የየወባ ትንኝ መከላከያ አጎበርም የለንም።በጎ ፈቃደኞች እዚህ ስንደርስ አንድ ኩባያ ሾርባ ሰጥተውን ነበር። ይህ ግን በቂ አይደለም። አሁን የዝናብ ወቅት ስለሆነ ለወባ እና ውሀ ወለድ በሽታዎች ተጋላች ነን። ወደ ማላዊ የተሰደድንበት ምክንያት ነፋሳችንን ለማትረፍ ነው። ምግብ መኝታ እንዲሰጠን ሙቀት ስለሆነም ከድንኳን ይልቅ የተሻለ መጠለያ እንዲፈለግልን የእርዳታ ጥሪ እናቀርባለን።»


ሌሎች ሴቶች ደግሞ ባሎቻቸው ጠፍተውባቸዋል። ምናልባት ወደ ማላዊ ይወስደናል ብለው የተሳሳተ መንገድ ሳይከተሉ አልቀሩም ብለው ይሰጋሉ። ኮሳ ወደ ማላዊና ኤስዋቲኒ እንደሄዱት ሌሎች ተፈናቃዮች  በሀገራቸeው ሰላም ሰፍኖ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ተስፋ ያደርጋሉ። የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማላዊና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች  ማላዊ ለተሰደዱት ሴቶች አዛውንቶች አካል ጉዳተኞች እና ህጻናት ደኅንነት ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጡ ተማጽነዋል። ሞሰስ ምካንዳዊር ኒያካ የተባለው የጥናት ተቋም ሃላፊ ፣የሞዛምቢክ ምክር ቤት አባላት፣ ተቃዋሚዎች 16 አባላት ካሉት የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ማኅበረሰብ ሳዴክና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ውይይት እና እርቅ እንዲካሄድ እንዲያበረታቱ ለዘላቂ ሰላምም እንዲሰሩ አሳስበዋል ።  
«እኔ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የምጠይቀው በሞዛምቢክ ሰላም እንዲወርድ የሳዴክ አባል የሆኑ ሀገራት የቀድሞ የመንግስታት መሪዎች  በአንድ ላይ ሆነው የሞዛምቢክ መንግሥትን ባለስልጣናት እና የተቃዋሚዎች መሪዎችን እንዲያናግሩ ነው። አሁን እኛ እንደ ሀገር ምን ማድረግ አለብን? ለተፈናቀሉት ምግብ ብርድ ልብስ እና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማቅረብ ምን ያስፈልገናል? ይህ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው። »

የሞዛምቢክ ወታደሮች በዋና ከተማይቱ በማፑቶ መንገዶች በጥበቃ ላይ
የሞዛምቢክ ወታደሮች በዋና ከተማይቱ በማፑቶ መንገዶች በጥበቃ ላይምስል Siphiwe Sibeko/REUTERS

 ሞዛምቢክን ያሸበረው ጥቃት

የማላዊ ባለሥልጣናት የሞዛምቢክ ስደተኞችን የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ለማጥናት ከተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህጻሩ UNHCR ጋር እየሰራ መሆኑን አረጋግጧል። ሆኖም ማላዊ የራሷን ዜጎችና አሁን በሀገርዋ የሚገኙ ቁጥራቸው ወደ 54ሺህ የሚጠጋ ስደተኖችን ለመመገብ በመታገል ላይ ያለች የምግብ እጥረት ያለባት ሀገር ናት።  ከስደተኞቹ አብዛኛዎቹም ከዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ከሩዋንዳ እና ከብሩንዲ የመጡ ናቸው። እነርሱም ማዕከላዊ ማላዊ ውስsxe በሚገኘው ድዛሌካ በተባለው የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ነው ያሉት። 


UNHCR በራሱ ከተመድ የምግብ መርሀግብር የገንዘብ ቀውስ ምክንያት ማላዊ የሚገኙ ስደተኞችን ለመመገብ መቸገሩ ደግሞ ጉዳዩን አወሳስቦታል። ስደተኞች የተጠለሉበት የንሳንዬ ቀበሌ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ሮበርት ናይያ ማላዊ ለተፈናቃዮቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጆንያዎች የበቆሎ ዱቄት እና ጥራጥሬዎችን ማቅረቧን ለስደተኞቹ መጠለያ ማዘጋጀቷንም ተናግረዋል።
«እስካሁን ለስደተኞቹ መጠለያዎች ሰጥተናል፤ ያቆየናቸው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ቦታዎች ነው። የአደጋ መከላከልና አስተዳደር መስሪያ ቤት ከ350 በላይ እያንዳዳንቸው 25 ኪሎ ግራም የሚይዙ ጆንያዎች የበቆሎ ዱቄት እና አተርም  ለስደተኞቹ ሰጥቷል። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የስደተኞች ጉዳይ ክፍል ደግሞ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ የማጥናት ስራ ይጀምራል።»የማሊታ ባናዳ ቀበሌ ነዋሪዋ ንሳንጄ የሞዛምቢክ መንግስት በተቻለ ፍጥነት አንድ ነገር እንዲያደርግ ተማጽነዋል። ምክንያቱም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ወደፊት በየቀኑ ምግብ ማግኘቱ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም።

ህዝቡ በቤንዚን ማደያዎች በሰልፍ ላይ
ህዝቡ በቤንዚን ማደያዎች በሰልፍ ላይ ምስል Amilton Neves/AFP

 ትኩረት በአፍሪቃ፤ የSADC ጉባኤ፣ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በሳሕል አካባቢ ሐገራት

የፍሬሊሞ ፓርቲ መሪ ዳንኤል ቻፖ በጎርጎሮሳዊው ጥር 15 በሞዛምቢክ ፕሬዝዳንትነት ቃለ መሀላ ይፈጽማሉ። ሕገ መንግሥታዊው ሸንጎ ቻፖ የጥቅምቱን ምርጫ 65 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን የተቃዋሚው እጩ ተወዳዳሪ ቬናንስዮ ሞንጄሎኒ ደግሞ 24 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን አስታውቋል። የምርጫ ውጤት ተጭበርብሯል የሚሉት ሞንጄሎኒ ዳግም ቆጠራ እንዲካሄድ የጀመሩትን ትግል እንደማያቆሙ ተናግረዋል። 

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ