በአሙሩ ወረዳ የሚደርሱ ጥቃቶች መበራከት
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 2 2017በ2016 ዓ.ም አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖበታል በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው በተመለሱበት የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰቱ የፀጥታ መደፍረሶች ነዋሪዎች መቸገራቸውን ተናገሩ። በአሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ እና አካባቢው በቅርቡ በተደጋጋሚ ችግሮች እየተፈጠሩ እንደሚገኙ እና በትናንትናው እለት በተከሰተው የፀጥታ ችግር በአሙሩ ወረዳ ዋሊሉቁማ በሚባል ቦታ አንድ የሚሊሻ አባል እና አንድ ሰላማዊ ሰው ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል ።
በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አስተዳደር መቀመጫ በሆነችው ሻምቡ ከተማ እና የተለያዩ ቦታዎች የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከዚህ ቀደም በየቤታቸው መመለሳቸውን የዞኑ አስተዳደር ዐሳውቋል፡፡ ከ40ሺ በላይ ሰዎች ከዚህ ቀደም ወደ ቤታቸው መመለሳቸው የተነገረው አሙሩ ወረዳ ሲትሆን በርካታ አርሶ አደሮችም በክረምት ወቅት ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን በግብርና ሥራ ላይ መሳተፋቸውም ተገልጸዋል፡፡
በጥቃቱ አንድ ሰላማዊ ሰው እና አንድ ሚሊሻ ሕይወት አልፈዋል
በዚህ አካባቢ በተለያዩ ወቅቶች የደፈጣ ጥቃቶችና እገታዎች እየተስተዋሉ እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በትናንትናው ዕለትም በአሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ አቅራቢያ ዋሊ ሉቁማ በሚባል ቦታ ጥቃት መፈጸማቸውን የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል። «በአንድ ሰላማዊ ሰው ላይ ነው ግድያው የተፈጸመው፡፡
ስለ አካባቢው ፀጥታ ውይይት ለማድረግ ታስቦ በተለያዩ ስም የሚንቀሳቀሱ በድኖች ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ፡፡ አሙሩ ወረዳ ብቻ ሳይሆን ጊዳ ኪረሙ ወረዳም አርሶ አደሮች በብዙ ቦታ በስጋት ግብርና ሥራ አቁመው ነበር፡፡ ብዙ ሰው ሥቃይ ውስጥ ነው ያለው፥ ወደ ከተማ አቅራቢያ የተመረተውን ምርት ለመሰብሰብም አርሶ አደሩ በስጋት ላይ ነው፡፡»
በአሙሩ ወረዳ የሚከሰተው የፀጥታ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ መቆየቱን የተናገሩት ሌላው የአካባቢው ነዋሪም ባንክን ጨምሮ በአካባቢው ብዙ ተቋማት ለዓመታት ተዘግቶ የቆዩት ሥራ ጀምሮ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ በታጣቁ ኃይሎች የሚደርሱ ጥቃቶችም አሁንም ዘላቂ መፍትኄ አለመግኙቱን በመጥቃስ በወረዳው የተከሰተውን የፀጥታ ችግር አብራርተዋል።
ነጋሣ ደሳለኝ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር