ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ፤ ተማሪዎች በምግብ ጥራት እና መጠን ላይ ያሰሙት ሮሮ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2017የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በምግብ ጥራት እና መጠን ላይ ያሰሙት ሮሮ
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “አዲሱ የምግብ ባጀት ተግባራዊ እንደሆነ ቢነገረንም የሚቀርብልን ምግብ በጥራትም ሆነ በመጠን የተሻሻለ ነገር የለም” ብለዋል። የተማሪዎች ህብረትም የተማሪዎ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ከመስራት ይልቅ እንቅፋት ሆኗል ነው ያሉት፣ ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ ባጀቱን ተግባራዊ ማድረግ እንዳልጀመረ አመልክቷል። የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡየተማሪዎች የቀን የምግብ ባጀትከነበረበት 22 ብር ወደ 100 ብር ማሳወቁን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ አንዳንድ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምንም አልተለወጠም ሲሉ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። ተማሪዎቹ የባጀቱ ዝርዝር የደረሳቸው ቢሆንም የምግብ አቅርቦቱ ከመሻሻል ይልቅ በጥራትም፣ በመጠንም ቀንሷል ሲል ነው አንድ ተማሪ የገለፀው። የቁረስ፣ የምሳና የእራት ጊዜ ምግቦች ምን፣ ምን ሊሆኑ እንደሚገባ ዝርዝር ከትምህርት ሚኒስቴር የመጣና ተማሪዎች እንዲያውቁት ቢደረግም ሳይሻሻል ቁርስ በሳምንት 4 ቀን ዳቦ እንደሚቀርብላቸው ተናግሯል። በአጠቃላይ ምግቡ እንኳን ሊሻሻል ከወር በፊት ከነበረው በሁሉም ረገድ ቀንሷል ሲል ነው የገለጠው።
“የምግብ ጥራትና መጠን ቀንሷል” ተማሪዎቹ
ተማሪዎቹ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በምግብ አቅርቦቱ ዙሪያ እንደተነጋገሩና እንደሚሻሻል ቢነገራቸውም ምንም ለውጥ እንደሌለ ነው ሌላው አስተያየት ሰጪ ተማሪ የተናገረው። ሌላ ተማሪም እንዲሁ ጠዋት የሚሰጠው የዳቦ አቅርቦት መጠኑም ሆነ ጥራቱ ከሚፈቀደው ጥራትና መጠን በታች ነው ብሏል። “ምንም ለውጥ አላገኘንም፣ ባለፈው ሰኞ የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ባለበት በምግብ ዙሪያ ተነጋግረናል፣ ይሻሻላል ብለው ፕረዚደንቱ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም አልተሻሻልም።” ነው ያለው።
“የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት አላገዘንም” ተማሪዎቹ
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረትም የተጣለበትን ኃላፊነት አልተወጣም ሲሉ ነው ተማሪዎቹ ቅሬታቸውን ያሰሙት። የተማሪ ህብረት ከተማሪዎቹ ጎን መቆም ነበረበት የሚሉት ተማሪዎቹ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ግን በተቃራኒው ነው እየሰራ ያለው ብለዋል፣ እንዴውም የዩኒቨርሲቲው ቅጥር ሠራተኛ መስለው ነው የሚንቀሳቀሱት ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጠዋል። የተማሪዎቹ ህብረት ፕረዚደንት እዮብ ክንዱ ድምፁ አየር ላይ እንዳይውል ጠይቆ የተማሪዎቹ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ግን እየሰራ እንደሆን አስረድቷል፣ በቀርቡም የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎችና ተማሪዎች ተቀራርበው እንዲወያዩ ማድረጉን አስረድቷል።
“የምግብ ዝርዝር ቢደርሰኝም አዲሱ ባጅት አልተለቀቀልኝም” የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አንድ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊ በበኩላቸው የትምህርት ሚኒስቴር የምግብ ዝርዝር ቢልክም ባጀት ተፈቅዶ አልተለቀቀም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አግማሴ ታረቅኝ መላሸንዲሰጡን ጠይቅናቸው ጉዳዩን የሚመለከተው ሌላ ሠው ነው በማለታቸው የትምህርት ሚኒስቴርን ሀሳብ ማካተት አልቻልንም።
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ