አወዛጋቢው የትግራይ ባለስልጣናት ሹመት እና የህዝብ አስተያየት
ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2017በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና የህወሓት አንድ ቡድን መካከል ያለው ውዝግብ እየተካረረ ባለበት በዚህ ወቅት፥ አንዱ ሌላውን በሕገወጥ መንገድ ስልጣን በመስጠት እየተወነጃጀሉ ይገኛሉ። በመቐለ ከተማ ምክር ቤት የተሾመ ከንቲባ በማገድ፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አዲስ ከንቲባ ለመቐለ መመደቡን ተከትሎ ውዝግቡ ሰሞኑን ይበልጥ የተካረረ ሲሆን፥ ይህን ተከትሎም የከንቲባው ፅሕፈት ቤት ታሽጓል። ከመቐለ ውጪም ዓዲግራት ከተማ እና ሌሎች የትግራይ ወረዳዎች እና ዞኖች ሁለት አስተዳዳሪዎች ተሾሞውባቸው ውዝግብ ላይ ናቸው። በዚህ ምክንያት መንግስታዊ አገልግሎት እየተደናቀፈ፣ በነዋሪው ላይም የፀጥታ ስጋት ፈጥሯል። በመቐለ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች፥ የህወሓት ባለስልጣናቱ ውዝግብ አሳሳቢ ይሉታል።
ትግራይ ክልል ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ ተገቢ ርምጃ ይወሰድ ተባለ
ለሁለት ተከፍለው ለረዥም ግዜ ውዝግብ ላይ የቆዩት የህወሓት አመራሮች፥ ባለፈው ነሓሴ ወር በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የፖርቲው ክፍል ጉባኤ ማድረጉ እና እንዳዲስ አመራር መምረጡ ተከትሎ ፍጥጫው ከሮ ቆይቷል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ያላገኘው እና ከፓርቲው ውስጥም ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ጉባኤ ያደረገው የህወሓት ቡድን፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጨምሮ በርከት ያሉ የማእከላይ ኮሚቴ አባላት ከፓርቲው ማገድ፥ በህወሓት ውክልና በግዚያዊ አስተዳደሩ ከያዙት ስልጣን ማውረዱ ያስታወቀው ደግሞ ባለፈው መስከረም ወር ነበር።
በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጉዳይ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ንግግር ላይ እንዳለ የሚገልፀው ህወሓት፥ በተለያዩ ከተሞች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች ግን እጩዎች ለምክርቤቶች እያቀረበ ሹመቶች እያፀደቀ ነው። በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክፍል በተለያዩ ከተሞች እና ወረዳዎች ያሉ ምክርቤቶች ላልተፈለገ ዓለማ እየተጠቀመ ነው፣ መፈንቅለ መንግስት እያደረገ ነው፣ ግዚያዊ አስተዳደሩ እንዳይረጋጋ እና ስራው እንዳይከውን እየተንቀሳቀሰ ነው በማለት በተደጋጋሚ የሚከሰው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በበኩሉ፥ በምክርቤቶች የተላለፉ ውሳኔዎች በማገድ ተጠምዷል።
ትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚፈፀም ፆታዊ ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል
በቅርቡ በመቐለ ከተማ ምክርቤት አፅዳቂነት የከተማዋ ከንቲባ ተደርገው የተሾሙት ዶክተር ረዳኢ በርሃ ያገደው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ አቶ ብርሃነ ገብረየሱስን በከንቲባነት የመደበ ሲሆን፥ በዚህ መካከል በተፈጠረ ውዝግብ የከተማው ከንቲባ ፅሕፈት ቤት ታሽጓል። ተመሳሳይ ሁለት ባለስልጣናት ለአንድ ቦታ የመሾም አጋጣሚ በቅርቡ በዓዲግራት ከተማ ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ዞኖች እና ወረዳዎች ተስተውሏል። በዚህም ምክንያት መንግስታዊ አገልግሎት እየተደናቀፈ፣ በነዋሪው ላይም የፀጥታ ስጋት እየተፈጠረ ነው። በመቐለ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች፥ የህወሓት ባለስልጣናቱ ውዝግብ አሳሳቢ ይሉታል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ