የቤንዚን እጥረት በጋምቤላ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23 2017
የቤንዚን እጥረቱ 6 ወራትን አስቆጥሯል።
የቤንዚን እጥረት በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ዋና ችግር ከሆነ ሰነባብቷል። ችግሩ ካጋጠማቸው አካባቢዎች አንዱ የጋምቤላ ክልል ሲሆን እንደአስተያየት ሰጪዎቹ በጋምቤላ ክልል የቤንዚን እጥረት ከተከሰት 6 ወራትን አስቆጥሯል። በዚህም በዋናነት የሥራቸው ባህርይ ከቤንዚን ጋር የተያያዘ ሠዎች አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለመስጠት መቸገራቸውን ነው የሚገልፁት።
አንድ አሽከርካሪ ቤንዚን አጎራባች ክልል ከሆነው ኦሮሚያ ክልል አንድ ሊትር እስክ 600 ብር ገዝተው ለመጠቅም መገደዳቸውን ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል።
ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በቂ የነዳጅ ማደያዎች በክልሉ ቢኖሩም በህገወጥ መንገድ ነዳጅ መሸጡን ስለሚመርጡ ባለማደያዎች ህጋዊ በሆነ መልኩ ለተጠቃሚው እንደማይቀዱ ተናግረዋል። በመሆኑም በየመንገዱ በህገወጥ መንገድ ተደርድረው ከተቀመጡ በሐይላንድ ላስቲክ ከተሞሉ ጠርሙሶች ቤንዚን በውድ ዋጋ እንደሚገዙ አመልክተዋል።
የቤንዚን ግብይቱ በህገወጥነት ተተብትቧል
ሥማቸው እንዳይጠቀስና ድምፃቸው አየር ላይ እንዳይወል ያስጠነቀቁን አንድ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ“የነዳጅ ግብይቱ በከፍተኛ ሁኔታ በሙስናና በህገወጥነት ተተብትቧል” ብለዋል። የትራንስፖርት ተጥቃሚው ህብረተሰብ የትራንስፖርት ታሪፉ ከፍተኛ በመሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎት እያገኘ እንዳልሆንም አብራርተዋል።
“የቤንዚን እጥረት ቢኖርም ህገወጥነት የለም” የክልሉ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ኛሞች ጊል
የጋምቤላ ክልል ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ኛሞች ጊል በክልሉ የቤንዚን እጥረት መኖሩን ጠቅሰው ምክንያቱ ደግሞ የሚመጣው ነዳጅ በአብዛኛው በክልሉ ወደሚገኘው የወርቅ ማወጫ ፋብሪካ ስለሚሄድ ነው ብለዋል።
ህገወጥ የቤንዚን ግብይት በክልሉ የለም ያሉት ወ/ሮ ኛሞች እጥረቱን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከሩበት እንደሆነ ገልፀዋል።
“በክልሉ ላልው የቤንዚን እጥረት ምክንያቱ ኮንትሮባንድ ንግድ ነው” የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን
የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ በቀለች ኩማ እንዳሉት ደግሞ በክልሉ ላለው የቤንዚን እጥረት ዋናው ምክንያት የኮንትሮባንድ ንግድ ነው። የሚታዩ ችግሮች በየወቅቱ እንዲፈቱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከየክልል ንግድ ቢሮዎች ጋር በየሶስት ቀኑ ውይይት እንደሚያደርግ ጠቅሰው በጋምቤላም ከነዳጅ ጋር በተያያዘ አዲስ ነገር ካል በዚሁ መንገድ እንደሚፈታ ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ አንዳንድ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶችን ለማነጋግር ያደረግ ነው ጥረት ሰልአልተሳካም።
በጋምቤላ ክልል እስከ 5 ሺህ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ቢኖሩም ህጋዊ ታርጋ ቁጠር ኖሯቸው የሚንቀሳቀሱት ከ3 ሺህ እንደማይበልጡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ