የነዳጅ ዋጋ መጨመር ያስከተለው የዋጋ ንረት
ዓርብ፣ ጥር 9 2017
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት ባወጣው የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ አንድ ሊትር ቤንዚን ላይ የ10 ብር ጭማሪ ተደርጎ 101.47 ብር እየተሸጠ ነው። ነዳጅ አጠቃላይ የምጣኔ ሐብት እንቅስቃሴዋ መሠረታዊ ሸቀጥ የሆነባት ኢትዮጵያ እንዲህ ያለው እርምጃ ተጽዕኖው ሌሎች ዘርፎችንም ይነካል። የአፋር ክልል ነዋሪው ወጣት እንዲያም ሆኖ ቤንዚን የሚሸጥበት ዋጋ በብዙ እጥፍ ነው ይላል።
«ቤንዚን የትራንስፖርት ችግር ስላለ 600 ብር ነው ሊትር።»
ይህም በመሆኑ ምክንያት በፋብሪካ ውጤቶች ላይም ሆነ በግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል ሲል ይገልፃል። «50 ብር የነበረ ትራንስፖርት ሁለት መቶ ብር ገብቷል» ብሏል። አልፎም ሩዝ፣ ጤፍ ፣ ነጭ ዱቄት ሁሉ ጨምሯል ነው ያለው።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የበላይ ሀላፊ ነስረላ አብዱላሂ ነዳጅ በታሪፍ እየተሸጠ አለመሆኑን አምነው አንድ ሊትር ቤንዚን ከ300- 600 ብር ይሸጥ እንደነበር ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።
የደቡብ ጎንደሩ ነዋሪ አሁን ላይ ያለው የትራንስፖርት ሥራ ትርፉ ድካም ነው ይላል። «እስከ 600 ብር ገብቷል ሁለት ሊትር። ቢቆም ይሻላል [ሥራው]» ሲል መልሷል።
በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማራው ይሄው ግለሰብ ከከተማ ወጣ ብሎ መሥራቱ በአካባቢው ካለው ግጭት መነሻ ሥጋት በመኖሩ ያንን ማድረጉን እንደማይደፍርም ገልጿል።
«ሁለት ሳምንት ይሆናል ካቆምኩ [ተሽከርካሪየን]።»
የሀዋሳ ከተማ ነዋሪውም ተመሳሳይ የነዳጅ እጥረት የፈጠረው የሥራ መዳከም ችግር እያስተናገዱ መሆኑን «መሥራት አልቻልንም» ሲል ገልጿል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ምኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ከወር በፊት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ «የምርት ነፃ ዝውውርን የሚገድቡ» ያሏቸው 283 ሕገ ወጥ የከተማ በር ወይም መቅረጫ ኬላዎች በመላው ሀገሪቱ መኖራቸውን ከነዳጅ እጥረቱ ባለፈ የኑሮ ውድነት አባባሽ ያሉትን ገልፀው ነበር።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ ዛሬ ዓርብ በሰጡት መግለጫ «የሸቀጥ ዝውውር ገደብ እንዳይኖር መንግሥት እርምጃ ወስዷል»። ብለዋል።
በዛሬው ዕለት ከአራት ኪሎ መገናኛ እስከ ሲ ኤም ሲ በተመለከትናቸው አምስት የነዳጅ ማደያዎች አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት ሁለቱ ብቻ ናቸው። አንደኛው ላይ ከዚህ በፊት ይስተዋል የነበረው ረጅም ሰልፍ አሁንም በጉልህ ይታያል። የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ነዳጅ የመጨመሩ ጉዳይ አሁንም አይቀሬ መሆኑን ጠቁመዋል።
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በአጠቃላዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው ከዚህ በፊት ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮች ዋጋ ይጨምራሉ፤ እህል የሚያመጣውም፣ ኑሮ ስለተወደደ ብሎ የቤት አከራዩም የዋጋ ጭማሪ ሊያደርጉ ይችላሉ ብለዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ