«የከንቲባ ያለህ» የመቐለ ነዋሪዎች አቤቱታ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23 2017በህወሓት ሁለት ቡድኖች መካከል የተፈጠረ ውዝግብ ተከትሎ የመቐለ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅሕፈትቤት ከታሸገ አንድ ወር ሆነው። ዛሬ ጠዋት በመቐለ ሰልፍ ያደረጉ ወጣቶች በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የተሾመ ከንቲባ ስራው እንዲጀምር ጠይቀዋል። ሰልፉ በተካሄደበት ስፍራ ከፍተኛ ቁጥር ያለቸው ፖሊሶች እና ሌሎች የፀጥታ ሐይሎች ከበውት የነበረ ሲሆን፥ ተጨማሪ ሰልፈኛ ወደ አካባቢው እንዳይጠጋም በየአቅጣጫው ክልከላ እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል።
በህወሓት ሁለት ቡድኖች መካከል ያለው ክፍፍል ተከትሎ ሁለት ከንቲባዎች የተሾሙባት መቐለየአስተዳደር ክፍተት ተፈጥሮባት ይገኛል። በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን በዋነኝነት በሚቆጣጠረው የመቐለ ከተማ ምክርቤት በኩል ዶክተር ረዳኢ በርሃ የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሆነው እንዲሰሩ ባለፈው ጥቅምት ወር አፀድቆ የነበረ ሲሆን፥ ይህ የተቃወመው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ደግሞ አቶ ብርሃነ ገብረየሱስ የመቐለ ከንቲባ ሆነው እንዲሰሩ ባለፈው ሕዳር 22 ቀን 2017 ዓመተምህረት ሹመት ሰጥቶ ነበር። ይህ የተፈጠረው የሁለት ከንቲቦች ውዝግብ ተከትሎ በመቐለ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ያለው የከንቲባ ፅሕፈት ቤት ከአንድ ወር በፊት በፀጥታ ሐይሎች ታሽጓል። መቐለም አንድ ወር ሙሉ ከንቲባ አልባ ከተማ ሆናለች። ዛሬ ጠዋት በመቐለ፥ ለትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ድጋፋቸው የሚሰጡ፣ በግዚያዊ አስተዳደሩ የተሾሙ ከንቲባ ስራቸው እንዲጀምሩ የሚጠይቁ እንዲሁም የትግራይ የፀጥታ ሐይሎች ከፖለቲካዊ ውግንና ነፃ እንዲሆኑ የሚገልፁ መፈክሮች ያሰሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በመቐለ ከተማ አስተዳደር ህንፃ አካባቢ ሰልፍ አካሂደዋል።
በዋነኝነት ሰልፍ በተካሄደበት ስፍራ ከፍተኛ ቁጥር ያለቸው ፖሊሶች እና ሌሎች የፀጥታ ሐይሎች ከበውት የነበረ ሲሆን፥ ተጨማሪ ሰልፈኛ ወደ አካባቢው እንዳይጠጋም በየአቅጣጫው ክልከላ እንደነበረ ለመረዳት ችለናል። ሰልፈኞቹ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ውሳኔ ይከበር፣ ከንቲባ ብርሃነ ገብረየሱስ ወደ ቢሮአቸው ገብተው ስራቸው ይከውኑ፣ ታጣቂዎች ከአስተዳደር መስርያቤት ይውጡ ወደ ካንፖቻቸው ይገቡ የሚሉና ሌሎች በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን የሚወቅሱ መፈክሮች ተስተጋብተዋል።
ከሰልፈኞቹ መካከል ያነጋገርናት ገነት ወልደስላሴ "እየጠየቅን ያለነው ከንቲባ ስራው እንዲጀምር ነው። በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የተሾመ ከንቲባ ስራው ሳይጀምር ከአንድ ወር በላይ አልፏል። በጌታቸው ረዳ የተሾሙ ከንቲባ ስራቸው እንዳይሱ ተከልክለዋል። ለዚህም ምንም ምክንያት የለም። በሰላማዊ መንገድ ነው እየጠየቅን ያለነው። መቐለ ትልቅ ከተማ ነው። ከወር በላይ የከንቲባ ቢሮ ታሸገ ማለት አሳፋሪ ነው" ብላለች።
ከዚህ በተጨማሪ ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ግዜ መቐለ ከንቲባ አልባ መሆንዋ ተከትሎ ግልፅ የአስተዳደር ክፍተት እየታየ ነው ሲሉ ሌላው ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪ አቶ በርሀ አርአያ ተናግረዋል።
ይህ ሁኔታ ተከትሎ መቐለ ከትላንት ጀምሮ ከፍተኛ የፀጥታ ሐይሎች ቁጥር በየመንደሩ ይታይባታል። ውጥረት ከሚታይበት የመቐለ ከተማ አስተዳደር መስርያቤት በተጨማሪ ሮማናት አደባባይ እና በሌሎች የከተማዋ ክፍሎች በርከት ያሉ ታጣቂዎች ተሰማርተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ትኩረቱ ያደረገ ስብሰባ ዛሬ ጠዋት ማካሄድ መጀመሩ የክልሉ ኮምኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል። በዚህ ስብሰባ የክልሉ ካቢኔ አባላት፣ የሰራዊት አመራሮች፣ የዞኖች መሪዎች እየተሳተፉ መሆኑ ከተሰራጨው መረጃ ታዝበናል። ዝርዝር ጉዳዮች በቀጣይ ይገለፃሉ ተብሏል። ዛሬ በተካሄደው ሰልፍ ከመቐለ አስተዳደር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ