1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕላስቲክ ብክለት የሁሉም ስጋት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 13 2016

በየቦታው የሚጣለው ፕላስቲክ ያስከተለው ብከለት የመላው ዓለም ችግር ከሆነ ሰነባበተ። በየዓለመቱ ከ19 እስከ 23 ሚሊየን ቶን የሚገመት የፕላስቲክ ቆሻሻ በወንዞች፣ በባሕሮችና ሐይቆች ባጠቃላይ ወደ ውኃ አካላት እንደሚጣሉ የተመድ የአካባቢ ጥበቃ መርሐግብር መረጃ ያመለክታል።

https://p.dw.com/p/4g7Lp
 ፎቶ ከማኅደር፤ የፕላስቲክ ዕቃ መያዣዎች በቻይና ገበያ
በየሀገሩ በርካቶች የፕላስቲክ ዕቃ መያዣዎችን መጠቀማቸው የተለመደ ሆኗል። ፎቶ ከማኅደር፤ የፕላስቲክ ዕቃ መያዣዎች በቻይና ገበያምስል Getty Images/AFP/Teh Eng Koon

ጤና እና አካባቢ

የፕላስቲክ ቆሻሻዎች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በርካታ ሃገራትም አሳሳቢ ችግር ችግር ሆኗል። እንደጀርመን ባሉት ሃገራት የዕቃ መያዣ ላስቲኮችን ለማስቀረት ኪስ ወረቀቶችና የወረቀት ቦርሳዎችን በብዛት ጥቅም ላይ ከማዋል አንስቶ፤ ሰዎች አንዴ ከየሱቁ ያገኙትን የዕቃ መያዣ እንዳይጥሉ ዋጋ በማስከፈል እንዲጠነቀቁ ለማድረግ ይሞክራሉ። በዚህ ምክንያትም የጨርቅም ሆነ ከወረቀት የተዘጋጁ የዕቃ መያዣዎችን በቦርሳም ሆነ መኪና ይዞ መንቀሳቀስ የተለመደ ነው። የተመድ የአካባቢ ጥበቃ መርሐግብር እንደሚለው በየዕለቱ በሁለት ሺህ የቆሻሻ መጫና ግዙፍ ተሽከርካሪዎች የሚሞላ የፕላስቲክ ቆሻሻ ወደ ወንዞች፣ ሐይቆች እና ባሕሮች ውስጥ ይጣላል። በዚህ መነሻነትም በዓመት ወደ ተለያዩ የውኃ አካላት የሚገባው የፕላስቲክ ቆሻሻ መጠን ከ19 እስከ 23 ሚሊየን ቶን እንደሚደርስም ያመለክታል።

ሰሞኑን ይፋ የሆነ መረጃ ደግሞ እንደሚያመለክተው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በዓመት 80 ሺህ ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻ ይጣላል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ የፕላስቲክ ብክለት ለዋና ከተማዋ አሳሳቢ ነው ይላሉ። «ለዚህም በዋነኛነት በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ ነው።» የሚሉት አቶ ዲዳ ኅብረተሰቡ የሚጠቀምበት ፕላስቲክ በአግባቡ ካልተጣለ ቱቡዎችን የመዝጋት እንዲሁም የውኃ አካላትንም የመበከል አጋጣሚው እንደሚሰፋና ዳግም ሰው ወደሚመገበው የምግብ ሰንሰለት የመግባት እድል እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ስለፕላስቲክ ቆሻሻ አወጋገድና ሊገኝ ስለሚችለው ጥቅም የአቶ ሲሳይ ክፍሌ ያሳተሙት መጽሐፍ
ስለፕላስቲክ ቆሻሻ አወጋገድና ሊገኝ ስለሚችለው ጥቅም የአቶ ሲሳይ ክፍሌ ያሳተሙት መጽሐፍ የሽፋን ገጽ። ምስል Sisay Kifle

 

በኬሚስትሪ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዳላቸው የገለጹልን አቶ ሲሳይ ክፍሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ በሚባለው የፕላስቲክ ፋብሪካ ውስጥ መሥራታቸውን ይናገራሉ። «የፕላስቲክ ውዳቂን ወደ ጥቅም በመቀየር የአካባቢ ብክለትን መቀነስ» በሚል ርዕስ መጽሐፍ የጻፉ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ የሆኑትን አቶ ሲሳይ በኢትዮ ፕላስቲክ ፋብሪካ ቆይታቸውም የፕላስቲክን አመራረት፤ አሠራሩን ጥሬ ዕቃውን ጭምር በቅርበት የማየትና የመረዳት እድል አግኝተዋል። አጋጣሚውም ስለፕላስቲክ እንዲያጠኑና እንዲመራመሩ ሁኔታውን ስላመቻቸላቸው ከተረዱት በኋላ ስለፕላስቲክ መናገርና መጻፍ መጀመራቸውን አጫውተውናል። ስለፕላስቲክ እርስዎ የተረዱትን ምስጢር አካፍሉን ያልናቸው አቶ ሲሳይ፤ «ፕላስቲክን በሚገባ ስናውቀው ስንረዳው በጣም ጠቃሚ ነገር እንዳለው እንረዳለን» ነው ያሉት። እሳቸው እንደሚሉት ከሆነው መጥፎ ነገሮች ቢኖሩትም ፕላስቲክ ጥሩ ጥሩ ነገሮች አሉት።

አቶ ሲሳይ እንደሚሉት የፕላስቲክ ቆሻሻ የዘፈቀደ አወጋገድ ችግር ማስከተሉ እየታየ ቢሆንም በተለያየ መልኩ እሱኑ ከመጠቀም መውጣት ግን አዳጋች ይመስላል። «መኪና ፕላስቲክ ነው፤ ፎም ፕላስቲክ ነው፤ ሞባይል ፕላስቲክ ነው፤ ቴሌቪዝን ፕላስቲክ ነው፤ ፍሪጅ (ማቀዝቀዣ) ፕላስቲክ ነው» በማለትም የምንጠቀምባቸውን ቁሳቁሶች ዘረዘሩ። እናም የፕላስቲክ ዕቃዎችን መጠቀም በቀላሉ የማይቀር ከሆነ ደረጃውን የጠበቀ ምርት እንዲኖርም ሆነ አወጋገዱ ላይ በስልት ቁጥጥር ማድረግ ይቻላል ባይ ናቸው አቶ ሲሳይ ።

 በዘፈቀደ የተጣለ የውኃ መያዣ ላስቲክ
በዘፈቀደ የተጣለ የውኃ መያዣ ላስቲክ ምስል Idrees Mohammed/AFP/Getty Images

አቶ ሲሳይ እንደነገሩን አዲስ አበባ ላይ ብቻ ከ900 በላይ ቆሻሻን ከየአካባቢው አሰባስበው የሚያስወግዱ ማሕበራት አሉ። በእነሱ አማካኝነት የሚጣሉ የተለያዩ ፕላስቲክ ነገሮች ተሰባስበው በተለያየ መንገድ ለዳግም ጥቅም ጭምር የሚውሉበት ሁኔታም መኖሩን ገልጸውልናል። የኅብረተሰቡም የፕላስቲክ አወጋገድ ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየታየበት እንደሆነም ታዝበዋል። በነገራችን ላይ አቶ ሲሳይ መጽሐፋቸው በዚህ ሥራ ለተሰማሩ ልጆች በአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ ኤጀንሲ አማካኝነት እንዲደርስላቸው መስጠታቸውን ነግረውናል።

የፕላስቲክ ቆሻሻ ብክለት በዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ ጎልቶ ይታይ እንጂ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ቢሆን ትልቅ ችግር እንደሆነ ከዚህ ቀደም ቦረና ውስጥ ከከብቶች ሆድ በቀዶ ጥገባ  በርካታ ኪሎ የሚመዝን የላስቲክ ክምችት ያወጡ የእስሳት ህክምና ባለሙያዎችን በዚህ ዝግጅት ማነጋገራችን ይታወሳል። ሰሞኑን ታዲያ የፕላስቲክ ብክለትን ለመቀነስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘመቻ መጀመሩን የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ገልጸውልናል። ለሰጡን ማብራሪያ እንግዶቻችንን እናመሰግናለን።

 ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ