የኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ
ቅዳሜ፣ መስከረም 26 2016ዲድ ዱባ ከምስራቅ ቦረና ዞን ዳስ ወረዳ ተነስተው ከ500 ኪ.ሜ. በላይ አቋርጠው ነው ኢሬቻን ለማክበር አዲስ አበባ የከተሙት፡፡ በእድሜ ጠና ያሉ ዲድ አባገዳም ናቸው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ ኢሬቻ መላው የኦሮሞ ህዝብ ከያቅጣጫው ተሰባስቦ ህብረት አንድነቱንም የሚያንጸባርቅብት መድረክ ነው፡፡ “ኢሬቻ የኦሮሞን ኃይል የሚያሳ ትልቅ መሰባሰቢችን ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጪም ኦሮሞ ተሰባስቦ የሚገናንበት ውበቱንም የሚያሳውቅበት ነው፡፡ ሃይማኖት እና ምንም ሳይበግረን አንድነታችን የማሳያ መድረክም ነው ኢሬቻ፡፡”
ይህ መድረክ አሁን ኦሮሞ ላጣው የተረጋጋ ሰላምም ኢሬቻ ትልቁ የመፍትሄ መነሻ ሊሆን ይችላል እንደ አዛውንቱ አስተያየት፡፡ “ሰላም ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አንዱ ልማት ሌላው ጥፋት እያሰበ መጓዝ አዳጋች ነው፡፡ ከውስጥም ከውጭም ነው ሰላም መሆን ያለብን፡፡ አሁን እንዲህ ተሰባስብን ተከባብረን ስንገኝ አምሮብናል፡፡ እዚህ ያለ ሰው ሁሉ ስለ ሰላም መጣራት አለበት፡፡ ሰላም ሲኖር ነው ሁሉም የሚሳካው፡፡ እናም እነም አንተም ሁላችንም ባለንበት ስለሰላም መስበክ ስለሰላም መጣራት አለብን፡፡”
ሌላኛዋ የበዓሉ ታዳሚም አስተያየታቸውን አከሉ፡፡ የሚያስቀና ያሉት ዛሬ እሬቻ ላይ የታየው ሰላምና አንድነቱ በመላው ህዝብ ዘንድ እንዲጋባ እና ሰላምን እንዲያሰፍንም ይሻሉ፡፡ “ከቦረና ዞን ነው በህብረት የመጣነው፡፡ የገርባ ኦረሞ ነን፡፡ ዛሬ ትንሽ ትልቁ እዚህ የተሰባሰቡት በመካከላችን ያለውን ልዩነት አውጥተው አንድነታችን ለማሳየት ነውና ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሁሌም እንዲህ ህብረታችን ብናጠናክር ጥላቻ እና በመሃላችን ያለው ግጭት ስለሚወገድ ያስደስታል፡፡”
የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ቅድ ባለሙያዎቹ እንስቶች
አረጋሽ ገዳ ደግሞ የኦሮሞ ሃዳ ሲንቄ ናቸው፡፡ ዛሬ በበዓሉ ላይ የታደሙት በትልቅ ደስታ እና ኩራት መሆኑንም በአስተያየታቸው አስረዱ፡፡ “ዛሬ በዓላችን እንደምታየው ደስ በሚል አኳሃን ነው የተከበረው፡፡ እንደምታየው ህዝቡም እንደወንዝ ነው ተጥለቅልቆ የወጣው፡፡ የወጣቱም መረጋጋት አስደናቂ ነው፡፡ ዛሬ በዓሉን ያከበረው ህዝብ ሰላሙንም እንደሚያሰፍን እጠብቃለሁ፡፡ እጅ ተያይዘን የአገራችን ሰላም እንድናረጋግጥ አደራ እላለሁ፡፡”
በዛሬው እሬቻ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከታደሙ የኦሮሞ ህዝብ በተጨማሪ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን የወከሉ ቡድኖችም በተሳትፎያቸው በዓሉን አድምቀውታል፡፡ ሰይፉ ለታ ከወላይታ ተነስተው ከሌሎች ጓደኖቻቸው ጋር ሆነው በዛሬ እሬቻ ከታደሙ ናቸው፡፡ “የሰላም ተምሳለት ወደ ሆነው ኢሬቻ የወላይታን ህዝብ ወክዬ በመሳተፌ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ እሬቻን ለማክበር ትናንት ከሰኣት ጀምሮ እዚህ ነን፡፡ ወጣቱ ሁሉ እያቀፌን ፎቶ እየተነሳ ፍቅር ነው ያሳየን፡፡ ይህን ሁሉ ህዝብ ፈጣሪ በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲመልስ ነው ጸሎቴ” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሽቶ ቦኪሳ ደግሞ የሲዳማ የባህል ቡድን ጋር ሆነው በኢሬቻ ከታደሙ ናቸው፡፡ እሳቸውም በያመቱ እንደሚታደሙበት የገለጹት እሬቻ አዲስ ነገራቸው ባይሆንም የዘንድሮው ይለያል ይላሉ፡፡ “ሰው ሰላም ወጥቶ ነው የሚገባው፡፡ ትልቅ ስነስርዓት ታያለህ ህዝቡ ላይ፡፡ የሰላም በዓል የሆነው ኢሬቻ በሁሉም ዘንድ ሰላምነ እንዲያመጣ ሁሉም ለራሱ ሲል ሰላምን ብያመጣ እላለሁ” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ስለ ኢሬቻ በዓል ዝግጅት ምን ይላሉ?
በአዲስ አበባ ውስጥ የሚከበረው ኢሬቻ-ሆራ ፊንፊኔ ለዓመታት ተቋርጦ እንደነበር ከተገለጸ በኋላ ዘንድሮ ለአምስተኛ ተከታታይ ጊዜ መከበሩ ነው፡፡ የዘንድሮ በዓሉ እጅግ ከፍተኛ ታዳሚያን የተሳተፉበት ሲሆን ፍጹም ሰላማዊም ነበር፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ