1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕላስቲክ ከረጢት አጠቃቀም ረቂቅ ሕግ እና የአካባቢ ጤና

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2017

ኢትዮጵያ ውስጥ የፕላስቲክ ከረጢት ወይም "ፌስታል" በሚል የሚታወቁ የፋብሪካ ምርቶችን መጠቀም፣ ማምረት ብሎም ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን የሚከለክል ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።ረቂቅ ሕጉ የፕላስቲክ ምርቶች የሚያደርሱቱን ዘርፈ ብዙ የጤና፣ የአካባቢ ብክለት፣ የንጽሕናና መሠል ተያያዥ ችግሮች ለማስቀረት ያለመ ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4oi0F
Äthiopien Plastiktüten
ምስል Solomon Muchie/DW

የፕላስቲክ ከረጢት አጠቃቀምን የተመለከተው ረቂቅ ህግ አና አንድምታው

የፕላስቲክ ከረጢት አጠቃቀም ረቂቅ ሕግ እና የአካባቢ ጤና 

 

ኢትዮጵያ ውስጥ የፕላስቲክ ከረጢት ወይም "ፌስታል" በሚል የሚታወቁ የፋብሪካ ምርቶችን መጠቀም፣ ማምረት ብሎም ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን የሚከለክል ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።ረቂቅ ሕጉ የፕላስቲክ ምርቶች የሚያደርሱቱን ዘርፈ ብዙ የጤና፣ የአካባቢ ብክለት፣ የንጽሕናና መሠል ተያያዥ ችግሮች ለማስቀረት ያለመ ነው ተብሏል።ኢትዮጵያ ውስጥ ፕላስቲክን የመጠቀም ልማድ ከማደጉ እና ሌሎች ተኪ አማራጮች ካለመኖራቸው ጋር ተያይዞ ይህንን ክልከላ የሚጥለው ሕግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ ቀጥሎ የሚነሳው ቁልፍ ጉዳይ ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ነው።

የፕላስቲክ ብክለት የሁሉም ስጋት

የረቂቅ ሕጉ ዝርዝር ጭብጦች ምን ይላሉ ?

ለኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ምክክር የተደረገበትና ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የተመራው ረቂቅ ሕግ "ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶች ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ" የሚከለክል ነው።ረቁቁ "የፕላስቲክ ከረጢት" የሚባሉ የኢንዱስትሪ ምርቶችን የተጠቀመን ወይም ለመጠቀም ይዞ የተገኘን ማንኛውም ሰው ለገንዘብ ቅጣት የሚዳርግ ጭምር ነው። ይህ ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያን የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ፣ ማጓጓዝ፣ ክምችት፣ መልሶ አጠቃቀም እና አወጋገድ ሥርዓት የማስያዝ ግብ ስለመያዙም ተነግሯል።

ይህ "የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ" ስድስት ክፍሎች እና 28 አንቀጾችን ይዟል።ዶክተር ፍራዖል ዋቆ የፕላስቲክ ምርትን በተመለከተ ጥብቅ ሕግ በምትከተለው ኬንያ አዋሳኝ ሞያሌ ከተማ የእንስሳት ጤና የሥራ ሂደት መሪ ናቸው። ባለሙያው በአካባቢው ቦረና ዞን ከዚህ በፊት 50 ኪሎ ግራም የሚመዝን ፕላስቲክ ከእንስሳት ሆድ ውስጥ የወጣበትን ክስተት በማስታወስ የሕጉ መውጣት ቢዘገይ እንጂ እጅጉን አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

የብክለት ሥጋት ያጠላበት የሀዋሳ ሐይቅ

"ሕጉ በጣም ጠቃሚ ነው። የአካባቢ ብክለትን ከመጠበቅ አንፃር፣ የአካባቢ ንፅህናን ከመጠበቅ አንፃር፣ በሰው ልጅ፣ በእንሥሳት እና በአፈር ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከመቀነስ አንፃር ሕጉ በጣም አስፈላጊ እና ሕጉ እንዲወጣ ስንናገር የነበረው ነው" ብለዋል።ከ18 ዓመታት በፊት የወጣውን "የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ"  የሚተካው ይህ ረቂቅ አዋጅ የፕላስቲክ ከረጢት ማምረትን፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን፣ ለገበያ ማቅረብን፣ መሸጥን ወይም ለንግድ ዓላማ ማከማችን ከመከልከሉ በላይ ያንን በሚያደርጉትም ላይ ከሃምሳ እስከ መቶ ሺህ ብር ቅጣትን የሚያስከትል ስለመሆኑ በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።ከዚህም አልፎ ሕጉን በሚተላለፉት ላይ "ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት" እንደሚያስቀጣ ደንግጓል።

ያለአግባብ የተወገደ የፕላስቲክ ከረጢት
"ሕጉ በጣም ጠቃሚ ነውምስል Solomon Muchie/DW

ቆሻሻ እንደ ሸቀጥ?

ጥፋቱ በድርጅቶች ላይ ሲሄን ደግሞ ቅጣቱ ሦስት እጥፍ እንደሚሆን በረቂቁ ሰፍሯል። ሆኖም አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በተመረተ፣ ወደ ሀገር ውስጥ በገባ፣ በሂደት ላይ ባለ ምርት ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን በአዋጁ ተጠቅሷል።ይህንን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠውም ለአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ከተሞች እስከ የገጠር መንደሮች፣ ከአነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች እስከ ትልልቅ የገበያ ማዕከላት የፕላስቲክ ከረጢት የሌለበት ቦታ የለም። የምግብም ይሁን የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስም ይሁን አነስተኛ መጠን ያላቸው የእህል እና የግብርና ምርቶች ግብይቶች ያለ ፕላስቲክ ከረጢት ወይም ፌስታል አይሆንም።

በፕላስቲክ ከረጢት የሚደረግ ግብይት
ጥፋቱ በድርጅቶች ላይ ሲሄን ደግሞ ቅጣቱ ሦስት እጥፍ እንደሚሆን በረቂቁ ሰፍሯል። ምስል Solomon Muchie/DW

"የካኪ ወረቀት ቢመጣ ጥሩ ነው። ያለ ፌስታልማ ምንም ነገር መግዛት አንችልም። ሕይወታችን ሁሉ ከፌስታል ጋር የተያያዘ ነው። ትንሽም ይሁን ትልቅ እቃ ይዘን የምንቀሳቀሰው በፌስታል ነው"

ለተፈጥሮ ጥበቃ የተወሰደው ርምጃ

የፕላስቲክ የፋብሪካ ምርቶችና ጉዳታቸው

የፕላስቲክ ምርቶች በልዩ ልዩ ዘርፍ አገልግሎት የመስጠታቸውን ያህል ጊዜያቸው እና ጥቅማቸው አብቅቶ ወደ ቆሻሻነት ሲቀየሩ ያን ጊዜ መሠረታዊ ችግሮችን ይዘው መምጣት ይጀምራሉ።ለረጅም ዓመታት ከአፈር ጋር ተዋህደው ወደ ብስባሽነት የማይለወጡ መሆኑ ቀዳሚው ገዳት ነው። ይህም እንደ የዘርፉ ባለሙያዎች ትንተና ለመሬት ምርታማነት ማጣት ምክንያት ይሆናሉ። እርሻን ያውካሉ። የአትክልትና እጽዋትን ዕድገትም ይገታሉ። አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች በየመንገድ ዳርቻዎች የታሸገ ውኃ መያዣ ፕላስቲክ ኮዳዎች እዚህም እዚያም የመታየታቸው ጉዳይ የሚያጠራጥር አይደለም። ከየቤቱ ከሚወጡ ደረቅ ቆሻሻዎች መካከል አብዛኛውም ፕላስቲክና ፕላስቲክ ነክ ቁሶች ይበዙበታል።

ወንዞች ላይ እና በዙሪያቸው ባሉ ዳርቻዎች እነዚህ ተረፈ ምርቶች አይጠፉም። የውኃ መፋሰሻዎች እና ቱቦዎች በሚያስጨንቅ ኹኔታ በፕላስቲክ ቆሻሻዎች መደፈንና መዘጋት ይገጥማቸዋል። ዶክተር ፍራዖል ዋቆ እነዚህ የፋብሪካ ውጤት የሆኑ ፕላስቲኮች የሚያደርሱትን ጉዳት ዘርዘር አድርገው ነግረውናል።"የከተማ ውበት ከማጥፋት እንዲሁም የተለያዩ የመፋሰሻ ሥርዓቶችን በመሙላት ከተሞች ለጎርፍ አደጋ እንዲጋለጡ የማድረግ፣ እንዲሁም በግብርናው በኩል የአፈር ብክለት ያስከትላሉ"

በፕላስቲክ ከረጢት የሚደረግ ግብይት
ወንዞች ላይ እና በዙሪያቸው ባሉ ዳርቻዎች እነዚህ ተረፈ ምርቶች አይጠፉም። የውኃ መፋሰሻዎች እና ቱቦዎች በሚያስጨንቅ ኹኔታ በፕላስቲክ ቆሻሻዎች መደፈንና መዘጋት ይገጥማቸዋል።ምስል Solomon Muchie/DW

ወንዞችን ከቡና ተረፈ ምርት ብክለት መከላከያ ዘዴ

መረጃዎች ስለ ፕላስቲክ አጠቃቀም ምን ያሳያሉ

ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የተገኙ መረጃዎች ( ቆየት ያሉ ቢሆንም ) ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢት በከፍተኛ ኹኔታ ጨምሯል።በ1999 የወጣው የደረቅ ቆሻሻ አዋጅ የሚመረቱ የፕላስቲክ ምርቶች ውፍረት ዝቅተኛ እና በስብሶ ከአፈር ጋር የሚዋሀድ እንዲሆን ይጠይቃል። ሆኖም ግን ሕጉን አክብሮ የሚያመርት ድርጅት ባለመኖሩ ብርቱ የአካባቢ ብክለትን አስከትሏል።እንደ ሀገር ከሚወገደው የቆሻሻ ክምችት ውስጥ ከ200 እስከ 250 ሺህ ቶን ከሚገመተው የፕላስቲክ ምርት መሆኑም ችግሩን አስከፊ እንደሚያደርገው ይነገራል።አሁን በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ማንኛውም ሰው ከመኖሪያ ቤት ይዞታው ድንበር አንስቶ ቢያንስ እስከ ሃያ ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማጽዳት ኃላፊነት ተጥሎበታል።የንግድ እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ደግሞ እስከ ሃምሳ ሜትር ርቅት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን እንዲያፀዱ ያስገድዳል።ረቂቅ ሕጉ ለመጽደቅ የመቃረቡን ያህል ውኃ፣ ዘይት የምግብ እና ሌሎች ምርቶች ማሸጊያዎችን ለመተካት ምን ታስቧል የሚለው ግን ምላሽ የሚያስፈልገው ነው።"አማራጭ የለንም። አንደኛ ለምደነዋል። ሁለተኛ አማራጭም የለንም። ፌስታልን የሚተካ ምርት እስካልመጣ ድረስ። ከዚህ በተጨማሪም ዋጋውም ቀነስ ያለ በመሆኑ ተቀባይነት ያለው ነው" 

ከተፈጥሮ ጋር ሰላም መፍጠር

ተለዋጭ ምርቶች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል

የፕላስቲክ ምርቶች ከፍተኛ ጉዳት ቢኖራቸውም ብዙ እና የማይናቅ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። ዕቃ መያዣዎችን ጨምሮ፣ የታሸጉ ምግቦች፣ መጠጥ እና ሌሌች ምርቶች፣ የቤት ውስጥ ወለል፣ መቀመጫዎች እና ሌሎችም።  እንዲህ ያሉ ድንጋጌዎች ሲረቀቁ ተለዋጭ ምርቶችን ማሰብ የግድ ይጠይቃል። እንደ ኬንያ ባሉት ጎረቤት ሀገራት ከጠንካራ ካኪ ወረቀቶች እና ከጨርቅ የሚዘጋጁ ምርቶች የፕላስቲክ ከረጢቶችን ተክተዋል። ሕብረተሰቡ ጉዳቱን መገንዘብ አለበት የሚሉት ዶክተር ፍራዖል መንግሥትም አማራጮችን   መፈለጉ ላይ ከወዲሁ እንዲያተኩር ጠይቀዋል።

ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር ዕይታ እና ተጨማሪ ሀሳቦች ተካተውበት እንዲቀርብ ለሚመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል። ተግባራዊ መሆን ሲጀምርም በዜጎች ጤና እና በሥነ-ምህዳር ላይ የሚደርሰው ጉዳት ይቀንሳልም ተብሎ ታምኗል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ