1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀዋር መሐመድ እና ወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምልከታው

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 21 2017

ከሰሞኑ በመገናኛ ብዙኃን የተከሰተው ጀዋር መሐመድ እንደገና አነጋጋሪ መሆን ችሏል። ከእስር ከተፈታ በኋላ ድምጹን አጥፍቶ የነበረው ፖለቲከኛው በራሱ ህይወት ዙሪያ የጻፈውን መጽሐፍ ለንባብ ከማብቃቱ ባሻገር በሚታወቅበት ድምጸት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና መንግስታቸው ላይ ብርቱ ትችት ማሰማት ጀምሯል።

https://p.dw.com/p/4oh56
Jawar Mohammed
ምስል Tamirat Dinssa/DW

የጀዋር መሐመድ ወደ ፖለቲካው መመለስ

የለውጥ ሰሞን በኢትዮጵያ

የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ የአራት ድርጅቶች ግንባር የሆነው ኢህአዴግ ሲፈርስ ኢትዮጵያ ወዴት እንደምታመራ በርግጥ ግልጽ አልበረም ። በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተማሪዎች ተጀምሮ ወጣቶችን ከዳር ዳር ያነቃነቀው ተቃዉሞ ገዢው ፓርቲንም ሆነ መንግስትን ፈተና ውስጥ አስገብተውታል። የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በዙሪያቸው ከነበረው የአመራር ተጽዕኖ ባሻገር በየአካባቢው የተቀጣጠለው እና ለበርካቶች ሞት እና ንብረት መውደም ምክንያት የነበረው አመጽ ያሳሰባቸውም ይመስላል ። ከውስጥም ከውጭም ብዙ ታገሉ ፤ ብዙ ደከሙ ፤ በመጨረሻ ግን ማድረግ የሚችሉት  አንድ ነገር ብቻ ሆነ። ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቅ። በወቅቱ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተቀጣጠለውን የወጣቶች አመጽ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በመምራት የሚታወቀው አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ በሀገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ የአንበሳውን ድርሻ መጫወቱን ይናገራል።  በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ እና ለውጥ እንዲመጣ ብርቱ ጥረት ያደረጉ የክልል አመራር እና ፖለቲከኞች ሚና ሳይዘነጋ ። ጀዋር መሐመድ ለሁለት ዓመት ገደማ ታስሮ ከወጣ በኋላ ከመገናኛ ብዙኃን ርቆ እና  ተለሳልሶ ከቆየ በኋላ አሁን እንደገና ተከስቷል። 

የፖለቲከኛ ጀዋር መሀመድ «የምስጋና ጉዞ» በጀርመን
 

የጀዋር ዳግም መከሰት

ከሰሞኑ በመገናኛ ብዙኃን የተከሰተው ጀዋር መሐመድ እንደገና አነጋጋሪ መሆን ችሏል። ከእስር ከተፈታ በኋላ ድምጹን አጥፍቶ የነበረው ፖለቲከኛው  በራሱ ህይወት ዙሪያ የጻፈውን መጽሐፍ ለንባብ ከማብቃቱ ባሻገር በሚታወቅበት  ድምጸት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና መንግስታቸው ላይ ብርቱ ትችት ማሰማት ጀምሯል። ታስሮ ከተፈታ በኋላ እንኳ  ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት እና ግጭት አልቆመም ።  የኑሮ ውድነትን ጨምሮ በርካታ ማህበራዊ ችግሮች ተባብሰው ሲቀጥሉ እርሱ ግን ዝምታን መርጦ ቆይቷል።  በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ከዶቸ ቬለ ጋር ቃለምልልስ ያደረገው ጀዋር ይህንን ጊዜ ለምን እንደመረጠ መልስ ሰጥቷል። 
 የእነ አቶ ጃዋር መሃመድ የህክምና ክርክር
ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጣ ከተባለ ማግስት አንስቶ ሰላም አልነበረም። በኦሮሚያ ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ፣ በደቡብ ፣ በሶማሌ እና አፋር አጎራባች አካባቢዎች ሺዎችን ለህልፈት ዳርገው ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅለዋል። 
በዓለማችን በቅርብ ጊዜ የጦርነት ታሪክ በአስከፊነቱ ከመጀመሪያዎቹ ተርታ ሊሰለፍ የሚችለው የትግራዩ ጦርነት  በትንሹ የአንድ ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት ሲነጥቅ ሶስት አስርት ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ወጪ እና የንብረት ውድመት አስከትሏል። ሲ,ወር,ድ ሲወራረድ የመጣ የረዥም ጊዜ ትርክን ጨምሮ ያለፉት አምባገነን መንግስታት ጥለዋቸው ባለፉ ብሎም በቀጠለው ሀገራዊ ቀውስ ፖለቲካዊ ንግግር በማድረግ ከስምምነት ሊደረስ አልተቻለም። ይህ ደግሞ ለብዙዎች ዕልቂት ምክንያት የሆነ ዕልቂት ከማስከተሉ ባሻገር አሁንም ድረስ መቋጫ አለማግኘቱ ይታያል።  
የሰሜኑ ጦርነት  እንዳይከሰት ብሎም ችግሮች በንግግር እንዲፈቱ ሲወተውቱ ከነበሩ ፖለቲከኞች መካከል ጀዋር መሐመድ ተጠቃሽ ነው ። ጀዋር በተለይ በፌዴራል መንግስቱ እና በትግራይ ክልል አመራር መካከል የተገባው እስጥ አገባ ሀገሪቱን ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል ባገኘው አጋጣሚ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል።

ፖለቲከኛ ጀዋር መሐመድ
የሰሜኑ ጦርነት  እንዳይከሰት ብሎም ችግሮች በንግግር እንዲፈቱ ሲወተውቱ ከነበሩ ፖለቲከኞች መካከል ጀዋር መሐመድ ተጠቃሽ ነውምስል Tamirat Dinssa/DW

የታጣቂዎች መመለስ እና የጀዋር ምልከታ
ጀዋር እነዚህን ጨምሮ ከውልደቱ ጀምሮ እስኪታሰር ብሎም ከእስር ወጥቶ ያደረጋቸውን እንቅስቃሴዎች ያሰፈረበትን መጽሐፉን ለንባብ አብቅቷል። በአማርኛ ፣ አፋን ኦሮሞ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች ለህትመት የበቃው መጽሐፉ 11 ክፍሎች ሲኖሩት የአማርኛው ጥራዝ የ409 ገጾች ያሉት ነው። 
አልጸጸትም የሚል ርዕስ የሰጠው እና ከልጅነት  እስከ ዕውቀት ያለፈባቸውን ዋና ዋና የፖለቲካ መስመሮች መለስ ብሎ የተመለከተትን መጽሐፉን ባለፈው ታህሳስ 10 ቀን ነበር ናይሮቢ ውስጥ ለማስመረቅ ቀጠሮ የያዘው። ነገር ግን ሳይጠበቅ  የምርቃት ስነስረዓቱ ተከለከለ። ጀዋር ለዚህ የኢትዮጵያን መንግስት ነው ተጠያቂ ያደረገው ።
የርሃብ አድማቸውን የገቱት ፖለቲከኞች የህክምና ሂደት
ፖለቲከኛው በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያቀረበውን ክስ መልስ እንዲሰጡበት ለመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚንስትሩ ለገሰ ቱሉ በእጅ ስልካቸው ላይ ደ,ውለን ነበር። ነገር ግን ሚንስትሩ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው በተደጋጋሚ ያደርግነው ጥረስ ሳይሰምር ቀርቷል። 
 መጽሐፉ በርካታ ጉዳዮችን አካቷል ። ለውጡ እና የለውጡ አመራር ጉዳይ ግን ለጊዜው ትኩረታችንን ስቧል።  ጀዋር በመጽሀፉ ገጽ 251 ላይ ለውጡን ማን ይምራው?  በሚለው ርዕስ ስር ባሰፈረው ሃሳብ አራት የለውጥ መሪዎች ዕጩዎችን ግምገማ በዝርዝር መመልከቱን ያትታል።  አራቱም የኦሮሞ ብሔር እና የኦህዴድ ኦዴፓ አባላት ናቸው ። 
በመጀመሪያ የተቀመጡት የቀድሞው የጦር ጄኔራል፤ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የነበሩት  አባዱላ ገመዳ ሲሆኑ ግምገማው
፣ ከፍተኛ የፓለቲካ ብስለት ያለው እና ሽግግሩን ለመምራት ከሁሉም የተሻለ ዝግጅት ቢኖረውም በአመራርነት ላይ ለረጅም ጊዜ ሰለቆየ እና ለሰፊ ፐሮፓጋንዳ ስለተጋለጠ በሕዝቡ ዘንድ እንደ ለውጥ መሪ (change agent) ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም። ይላል።

የእነ አቶ ጃዋር የክስ ሂደት

የለውጥ አመራሩ እና የጀዋር ግምገማ
ሁለተኛው የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ወርቅነሀ ገበየሁ ሲሆኑ ፡ ሰዎችን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስተባብሮ ለመምራት የሚያስችል ሰብዕና እንዲሁም ረዘም ያለ የአመራር ልምድ ሰላለው ሸግግሩን መምራት ያስችለዋል። ነገርግን አሱም ነባር አመራር ስለሆነ እንደ አዲስ አመራር ሕዝቡ እንዲቀበለው ማድረግ ይከብደናል። ይላል ግምገማው።
ሶስተኛው በወቅቱ የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበር (የአሁኑ ጠ/ሚኒስትር) ዐቢይ አህመድ ናቸው  ። የዐቢይ አሕመድ ግምገማ   ፣ ከዚህ በፊት ብዙም የማይታወቅ እና አዲሰ ፊት መሆኑ 'የለውጥ መሪ' አድርጎ ማቅረቡ ሕዝቡን ለመሳብ ይጠቅማል። በዕድሜ ከሌሎቹ ወጣት መሆኑ በቄሮዎች ዘንድ ተቀባይነት አንዲኖረው ያደርጋል፣ ነገር ግን በቅርብ ብቅ ያለ ሰለሆነ ችሎታው፣ ባሕርይው እና አመለካከቱ አይታወቅም። ችሎታው እና አመለካከቱ በተጨባጭ ሥራ ላልተፈተነ ሰው ውስብሰቡን የፖለቲካ ሽግግር ኃላፊነት መስጠት ከፍተኛ አደጋ (risk) ሊኖረው ይችላል። ይላል።

ጀዋር መሐመድ
የለውጥ አመራሩን ገምግመናል ምስል Mulugeta Ayene/AP Photo/picture alliance

በሐጫሉ ግድያ የተጠረጠሩና የእነ አቶ ጀዋር የፍርድ ሒደት
አራተኛው ሰው የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ናቸው።  ግምገማው እንደሚለው አመራርነት ውስጥ በመቆየት ጥሩ ልምድ አካብቷል፣ ትዕግሥት እና ብስለትም እንዲሁ ታድሏል። በንግግሩ እና ተክለ ስብዕናው የሀገር መሪነት ግርማ ሞገስ ይታይበታል። ወደ ፐሬዝዳንትነት የመጣው በቅርቡ ሰለሆነ በፐሮፓጋንዳ አልተጠቃም። ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ለቄሮ ትግል አለኝታነቱን በግልጽ በማሳየቱ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሎታል። ሲል ይገልጻቸዋል።  የፖለቲካ አቋሙ ለዘብተኛ (moderate) ስለሆነ ሌሎች ብሔሮችን ለመሳብ ይረዳል። ድክመቶቹ የማደራጀት ችሎታ እና በቆራጥነት መወሰን አለመቻል ናቸው።ም ይላል። በጃዋር መሐመድ መጽሀፍ ውስጥ የሰፈረው ግምገማ ።  ሆኖም ግን ይላል ሲቀጥል  እነዚሀን ክፍተቶች መዝጋት በሚችሉ ሰዎች በመክበብ ሽግግሩን እንዲያሳካ ማድረግ ይቻላል። ስለዚሀ ለማ የሽግግር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒሰትር ቢሆን ይሻላል የሚል መደምደሚያ ሰጥቷቸዋል።
ጀዋር ከዶቼ ቬለ ጋር በነበረው ቆይታ ካነሳቸው ጉዳዮች ይህንኒኑ ሃሳብ የሚያጠናክርበት ንግግር  ይገኝበታል።

አሁንም መቋጫ ያልተገኘለት ጦርነት 
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አሁንም ድረስ መቋጫ ያልተገኘላቸው ጦርነቶች እየተካሄዱ ነው። በኦሮሚያ ክልል መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰ,ራዊት አንድ ክንፍ (በጃል ሰኚ ነጋሳ) በሚመራው ኃይል በሰላም መግባት በክልሉ ብሎም ለሀገር ሰላም ሊያመጣ ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። ይህ ጥረት በቀጠለበት ወቅት ግን  ጀዋር  መሐመድ ወደ ፖለቲካው መድረክ በንቃት መመለስ ፤ ብሎም በመንግስት ላይ ትችት እና ዘለፋ ማድረስ ይህንኑ ጥረት ለማሰናከል ወይም አላስደስት ብሎት ይሆን ወይስ ለምን  ? ከዶቼ ቬለ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። 
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ለኢትዮጵያ መጻኢ ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ስለመሆኑ በስፋት ይነገራል። ነገር አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና እና ቁመና ወደ ፊት በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ ሊኖራቸው በሚገባ ሚና ላይ ጥያቄ ያስነሳሉ ። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውስጣቸው በሚፈጠር መከፋፈል ብሎም ከገዢው ፓርቲ በሚደርስባቸው ጫና መዳከማቸው ገዢውን ፓርቲ ምን ያህል ይገዳደራሉ የሚለው ጥያቄም መነሳቱ አይቀርም ።  ለዚህ ግን ጀዋር መሐመድ  የተለየ ምልከታ አለው። 

በእነ ጀዋር መሐመድ ላይ ምስክር ሊሰማ የነበረው ችሎት ለሌላ ጊዜ ተላለፈ
ኢትዮጵያ በብዙ ፈተና ውስጥ እያለፈቸ ሀገር መሆኗ ይታያል። በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጋር የሚያደርጉት ውግያ መቀጠሉ ፤ በኦሮሚያ ክልል አሁንም ድረስ መቋጫ ያልተገኘለት የኦሮሞ ነጻነት ሰ,ራዊት እና የመንግስት ዉግያ መቀጠል ፤ በየአካባቢው በታጣቂዎች የሚደረጉ ዕገታዎች የለት ተዕለት የሰላማዊዉን ዜጋ ህይወት ማቃወስ እና የኑሮ ውድነት ህዝቡ በተደጋጋሚ ሮሮውን የሚያሰማበት እና ዘላቂ እና ሰላማዊ መፍትሄ የሚሻበት ዋነኛ ጉዳዩ ሆኗል። 
የኢትዮጵያ መንግስት ነፍጥ ያስነሱ እና ሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ ያገኙ ዘንድ ሃገራዊ የምክክር መድረክ ለማድረግ ምዕራፍ በምዕራፍ እያስኬደ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል። 
ታጣቂ ቡድኖችን ጨምሮ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን ምክክሩ ከመሰረቱ ሁሉን አካታች አይደልም በሚል ሲተቹት ይሰማሉ ። ፖለቲ,ከኛ ጀዋር መሐመድ እንደሚለው ግን አሁን ቅድሚያ ማግኘት የሚገባው ሀገሪቱን ከውድቀት መታደግ ነው ።

ታምራት ዲንሳ